ረቡዕ 5 ማርች 2014

ግብረ ገብነት ሆይ ማደርያህ ከወዴት ነው!

ክፍል አንድ

እሪ በይ ኢትዮጵያ - ቅል ድንጋይ ሰበረ!
ውሃ ሽቅብ ወጣ - ዘመን ተቀየረ!
ሌባ እየከበረ - ነጋዴው ከሰረ!
ሀገር ፈራረሰች - ድንበር ተደፈረ!
እንደ ቅርጫ ስጋ - እየተመተረ!
ለአርብ ለድርቡሹ - ይታደል ጀመረ!
ጀግና አንገቱን ደፋ - ባንዳ ተወጠረ!!
(ግጥም፡ የማለውቀው ጸሀፊ)
******
ግብረ ገብነት ወይም የስነ ምግባር ትምህርትን ከማንም የበለጠ ከቤተሰቦቻችን እንማራለን፡፡ አንድን ነገር፣ ሀሳብ ወይም ድርጊት በጥሩና በመጥፎ፣ በጽድቅና በሀጢያት፣ በቅድስና እና እርኩሰት፣ … እየከፋፈልን የምናይበት ሂደት ነው- ግብረ ገብነት፡፡ እርግጥ ነው ለአንዱ ጽድቅ የሆነው ለሌላው ሀጢያት፣ ለአንደኛው የመልካም የሆነው ለሌላው መጥፎ አሊያም ደግሞ ለአንዱ ጥሩ ለሌላውም ጥሩ፣ ለአንድም ለሌላውም ጽድቅ ሆኖ የሚቆጠር ነገር ይኖራል፡፡ በነገሮች ላይ ያለን ጽንፍ አመለካከት ከባህል ባህል፣ ከቦታ ቦታ፣ ከሀይማኖት ተቋም ሀይማኖት ተቋም፣ ከቤተሰብም ቤተሰብ ሊለያይ እንደሚችል በዘርፉ በተለይም በስነ ባህል (Folklore) እና በ Cross Cultural Psychologists የተሰሩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
የግብረ ገብነትን ትምህርት በየትኛውም ህብረተሰብ ለማስረጽ የቤተሰብና የሀይማኖት ሚና ወሳኝ ነው፡፡ የሀይማኖት ተቋማት የማናየውን (በእምነት ብቻ የምናየውን) ዓለም ለመውረስ በጽድቅና ኩነኔ፣ በጥሩና መጥፎ፣ መካከል ያለውን ልዩነት ድንበር በማበጀት ለምዕመኖቻቸው አንድም በስብከት አሊያም ቅዱሳን ድርሰቶቻቸው ያስተምራሉ፡፡ እምነትም ያለስራ የተወገዘ መሆኑን አጽንተው ይሰብካሉ፡፡ ሰባኪውም በግብሩ ሞዴል የሆነለታ ጻድቅነት ይሰጠዋል -ወይ በአምላክ አሊያም በሰው፡፡
ይህ የግብረ ገብነት ትምህርት ከልጅነታችን ጀምሮ እየተማርን ስለምንመጣ የስብዕናችን አካል የመሆን እድሉ የሰፋ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ግብረ ገብ ለመሆን የግድ የተጻፈ ህግ ላያስፈልገን ይችላል፡፡ ህሊናችን በራሱ ችሎት መዝኖ ፍርዱን ይሰጠናል፡፡ ‹‹መጥፎ›› ስንሰራ ህሊናችን ሲቀጣን፣ ‹‹ጥሩ›› ስንሰራ ህሊናችን ‹‹ጎሽ›› ሲለን ከምድራዊው ህግ ይልቅ ሰማያዊውን ዓለም ስንናፍቅ፣ ሰማያዊውን አካል ስንፈራ ህይወታችን እንቀጥላለን፡፡ አንዳንዴ ታዲያ ይህችን ‹‹መጥፎ›› የሆነች ነገር ደጋግመን የሰራን እንደሆን ‹‹ሀጢያትነቱን›› እንረሳና እንደ ‹‹ጽድቅ›› በመቁጠር አሁንም እንቀጥላለን - ምንም እንኳ በሌላው ዘንድ ‹‹ህሊና ቢስ›› ብንባልም፡፡
ይህን የህግ ጥሰት የሚሰሩት ደግሞ ስለ ግብረ ገብነት የሚሰብኩና የሚያሰለጥኑ ግለሰቦችና ተቋማት ከሆኑ ‹‹ህሊና ቢስ›› በሚል ብቻ አይታለፉም- በምዕመኑ /ሰልጣኙ ‹‹አጃአይቭ›› ይባላል፡፡ ‹‹እነ እከሌ ያላከበሩትን እንዴት እኛ!›› የሚል ነገር ይነሳል፡፡ ከዚያም ጥሰቱ ይቀጥላል፡፡ በመጨረሻ ወደተቀደሰው ነገር ይቀላቀላል፡፡ ‹‹እርኩሱ›› ‹‹ቅዱስ›› ሆነ ማለት ነው - ‹በለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም› እንዲሉ፡፡ ህግ አውጪው ያልተገበረውን ህግ ፈጻሚው እንዴት ይቻለዋል!! በዚህ መልኩ ብዙ ነገሮች ከጊዜ ጊዜ ይቀያየራሉ፡፡ እነዚህ ለውጦች አንዳንዴ ሲጠቅሙን ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲጎዱን ይኖራሉ፡፡ ጥቅሙ አዲስ አስተሳሰብን በቶሎ እንድንላመድ፣ ያልታሰበን እንድናስብ ያደርገናል፡፡ ‹ንጉስ አይከሰስም ሰማይም አይታረስም› የሚለውን አስተሳሰብ ንጉሱን ለመገልበጥ በተደረገ ሙከራ ህብረተሰቡ ለካ ንጉስም ይቀየራል ወደማለት ይሸጋገርና በህዝብ የተመረጠ መንግስት ለመመስረት እንቅስቃሴ እንደሚጀመረው ሁሉ (ምንም እንኳ እስካሁን እኛ እድለኛ ባንሆንም -ባይሳካልንም)፡፡ ሰማይ አይታረስም የሚለውን አስተሳሰብ በአውሮፕላንና በሮኬት ወደ ህዋ ምጥቀት ህዋን ለማሰስ እንደተቻለው ሁሉ፡፡ ከዘመናት በፊት ‹‹የአስኮላ›› ትምህርት ‹‹የሰይጣን ነው›› የሚባለውን እንደረሳነው ሁሉ፡፡ ብዙ ነገሮች እንደቀየርናቸው ሁሉ፡፡
ብዙ ‹‹መጥፎዎች›› ወደ ‹‹ጥሩነት›› ተቀይረዋል፡፡ እኔን ዛሬ እንደጽፍ ያነሳሳኝ በስህተት ወይም በአለማወቅ ቀድመው ‹በሀጢያት› ተፈርጀው በኋላ ላይ ቦታቸውን ያገኙ እና ጥሩ ለውጥ ያመጡትን አስተሳሰቦችና ድርጊቶች አይደለም፡፡ በዚህ ሰበብ ከምርቱ ጋር የመጣ ገለባ እና ከስንዴው ጋር የተደበላለቀው እንክርዳድ ነው፡፡ እንዚህን ሊለዩ/ ሊያበጥሩ የሚችሉ መንሽና ማንካ ያነሳቸው የሞራል ገበሬዎች በርካታ እየሆኑ መጥተዋል፡፡
አንዳንዴ ስለሞራል ሳስብ እናቴንና አባቴን ሁሉ እስከመውቀስ የደረስኩበት ጊዜ አለ፡፡ አስታውሳለሁ እናቴ ‹‹የሰው ገንዘብ ቤታችንን አይከፍለውም›› የሚለውን ምክር ከሺህ ጊዜ በላይ ነግራኛለች፡፡ ገንዘብ ሳገኝ ለባለቤቱ እንድመለስ አሊያም ባለቤቱ ከጠፋ ‹ለኔ ቢጤ› እንድሰጥ ሆኜ ነው ያደግኩት፡፡ በልጅነታችን የምንጫወትባቸውን ድባና ቃጫ እንኳ ዛሬ ወድቆ ባለቤቱን ካገኘሁት እመለስ ነበር፡፡ የተገኘ ነው ለመባል አንድ እቃ ‹ጨለማ የነካው› (ጨለማ የነካው ማለት አንድ ሌሊት የማንም ሳይሆን ካደረና በቀጣዮቹ ባሉት ቀናት የተገኘ እቃ ለማለት ነው) መሆን ነበረበት፡፡ በልጅነቴ የተነገረኝ በተግበር ሳየው ሲጣረስ ጊዜ ይህን ጻፍኩ፡፡
ለመግቢያ ያክል ይህን ያክል ካልኩ የስነ ምግባር ችግር የምላቸውን አንድ በአንድ ለማየት እሞክራለሁ፡፡ በቅድሚያ ግን የሀይማት ተቋማት የሞራል ቀዳሚ አስተማሪ ስለሆኑ እንመለከታለን፡፡
1.   የሀይማኖት ተቋማት
‹አትስረቅ› ብሎ ያስተማራችሁ መምህር ሲሰርቅ ብትመለከቱ፣ ስለሰው ልጆች እኩልነት የሰበካችሁ እርሱ ጋንታ ሲለይ፣ የሰው ልጆችን እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ የሚለው ውስጡ በቂም የመገለ እንደሆነ ስትገነዘቡ ምን ይሰማችኋል!! እርግጥ ነው እነዚህ ግለሰቦች ራሳቸውን እንጅ የሀይማኖት ተቋሙን እንደማይወክሉ ግለጽ ነው፡፡ እኔ የምጽፈው የአየሁትን አሊያም እናንተ የምታውቁትን ሊሆን ይችላል -ግን ስንቶቻችን እንደሆነ አላውቅም፡፡ እስኪ አንዳንዶቹን አሁንም ዘርዘር አድርገን እንመልከት፡፡
1.1.  በታቦት ስም የሚለምኑ ሰዎች መበራከት
‹መዋሸት ሐጢያት ነው› እያለ የሚያስተምር፣ ስለስርቆት ወንጀልነት በየአብያተ ክርስቲያኑ የሚያስተምር ሰባኪ በየቦታው የቅዱሳንን ስዕል ዘርግቶ ‹‹እንዲህ የሚባል ቤተ ክርስቲያን ተቃጥሎ ለማሰራት … ከበረከቱ ተሳተፉ!!›› የሚል ጥሪ የሚሰጡ መንገድ ዘግተው የሚለምኑ ሰዎች በየከተሞቻችን መመልከት አዲስ አይደለም፡፡ በየቀኑ ቁጥራቸውም እየጨመረ ይገኛል፡፡ ከዚህ ላይ ለተባለው ዓላማ የሚለምኑ ሰዎች የሉም ማለት አይቻልም ግን በቁጥር አናሳ ይመስሉኛል፡፡ እያለው መለመን አንድ ችግር ነው ሲቀጥል ደግሞ በቅዱሳን ስም መለመን ሌላው ችግር ነው፡፡ እንበልና ያ የሚለምነው ሰው ገንዘብ ስለሌለው ብለን እንስብ፡፡ ታዲያ እንደኔ ቢጤዎች መንገድ ዳር ተቀምጦ መለመን ሲችል ስዕል ዘርግቶ ለሚለው ዓላማ የማይውልን ገንዘብ መሰብሰብ ‹ሐጢያትነቱ› ብዙ ነው፡፡ ውሸት አለበት፣ ስርቆት አለበት፣ አለመታመን አለበት፡፡ ለዚያውም ለእምነቱ በጣም ቅርብ ነኝ በሚለው ሰው (ለእምነቱ ቅርብ ያልሆኑ ሰዎች አስመስለው አይለምኑም ብሎ መደምደም አይቻልም)፡፡ ስጡ ይሰጣችኋል እያለ የሚያስተምረው ግለሰብ የሚሰበስበው ወደ ራሱ ኪስ ከሄደ ‹ቡራኬው› ምኑ ላይ ሊሆን ነው!! እነዚህን ግለሰቦች ማንም ወደ ህግ ሲያቀርባቸው አይታይም፡፡ የእምነቱ ሀላፊዎችም በእነዚህ ላይ ውግዘት ሲያደርጉ አሊያም ምዕመኖቻቸውን ሲያስተምሩ አይታይም፡፡ መስጠት አሪፍ ነው ብለን ስናስብ ለነማን መሰጠት እንዳለበትም ህዝቡን ማሳወቅ ያለብን ይመስለኛል፡፡  ለለመነ ሁሉ የሚሰጠው ከሆነ እና የሚለምኑ ሰዎች በአቋራጭ ሀብት የሚያካብቱበት አጋጣሚ ከበዛ ለማኝነትንም ማታለልንም አበረታታን ማለት ነው፡፡  ይህ ደግሞ የሚሆነው የግብረ ገብነትን ከሚያስተምሩት ወገን ሲሆን ችግሩን ለመፍታት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
1.2.  የንዋየ ቅድሳት ሽያጭ እና ስርቆት መበራከት
አስታውሳለው ከጥቂት አመታት በፊት በየመንገዱ ያለማንም ጠባቂ በደንብ ያልተቆለፉ ሙዳዬ ምጽዋት መስጫ ሳጥኖች ተተክለው ማዬት የተለመደ ነበር፡፡ አማኝም ያለውን ነገር ከዚያች አነስተኛ ሳጥን ውስጥ በደስታ ይጨምራል፡፡ ያችን ሙዳዬ ምጽዋት አይደለም መስበር ባለው ክፍተት የሳጥኗን መሙላት አለመሙላት መመለክት በራሱ በጠራራ ጸሀይ መብረቅ ወርዶ የሚመታን ይመስለን ነበር፡፡
አሁን በዱር የተቀመጠ ሳጥን አይደለም ከቤተ ክርስቲያን ጓሮ ያለ ሙዳዬ ምጽዋት እቃ ቤት ሳይቆለፍ በስህተት ቢያድር የሚፈጠረውን መገመት አያስቸግርም፡፡ የማይደፈሩ መስለው የሚታዩን ነገሮች ሁሉ በቅርብ ሰዎች ሲደፈሩ እናያለን፣ እንሰማለን፡፡ የአብያተ ክርስቲያናት ንብረት ብቻ ሳይሆን ጽላት ሁሉ የሚቸበችቡ ውስጥ አዋቂዎች የበረከቱበት ዘመን ላይ ነው ያለነው፡፡ በቀን ሰው በጨለማ ደግሞ ከአውሬ የባሱ ሰዎች ሞልተውናል፡፡ ቀን ላይ አውደ ምህረት ላይ ሲሰብኩ ላሳር፣ በቀለም እውቀታቸው የተደነቁ በግብር ግን ምንም የሌሉበት ሰዎች እንዴት ‹እምነት ያለስራ ከንቱ ነው!› ብለው ለመስበክ ሞራል የት አገኙ!! ቅርሳቸውንና ማንነታቸውን ለመሸጥ የማይደራደሩ ግለሰቦች እነርሱ እንዴት የሞራል አባት ሊሆኑ ይችላሉ!! እነዚህን ውድ ንዋዬ ቅድሳትና የሀገር ቅርሶችን ሊያሻሽጡ የሚችሉ ደላላዎች መበራከታቸው ለምን አይደንቅም!!  
የአራተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ አባቴ የት እንዳገኛት ባለውቅም አንድ ግጥም ነገረኝ፡፡ እኔም ከቤታችን በር ላይ በነጭ ጠመኔ ተየብኳት፡፡ ከ16 ዓመታት በኋላ ቤተሰብ ለመጠየቅ ስሄድ እስካአሁን ሳትጠፋ አገኘዋት፡፡ እንዲህ ትነበባለች!
ዝምድናም ተረሳ -ውለታም ባከነ
የሰው ሀይማኖቱ ገንዘብ ብቻ ሆነ!!
የሰውን ልጅ ገንዘብ ብቻ ሲነዳው ‹‹ለሁለት ጌታ አትገዙ›› እያለ የሚሰብከውን መምህር ገንዘቡ ሲገዛው አየን፡፡ ብዙ ሊባል ይችላል- ግን ምን ማድረግ ይቻላል!!
1.3.  የፍቅረ ቢጽ መጥፋት
ጓደኛህን እንደ ራስ ውደድ ብሎ ያስተማረ የሀይማኖት አባት እርሱን ያልመሰሉትን ሲያወግዝ፣ በሌሎች ላይ ሲዝት መመለከት የተለመደ ሆኗል፡፡ እኔ እስከማውቀው እርስ በርስ መዋደድን የሚኮንን እምነት ያለ አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ በክርስትና የሚጠሏችሁን ውደዱ ነው ዋናው ትዕዛዝ፡፡ የሚወደውን ማንም ይወዳል- የሚጠላውን መውደድ ከምንም በላይ እንደሆነ ነው መጽሀፍ የሚያዘው፡፡
ምንም እንኳ ይህ የብዙ ሰው ችግር ነው ብየ ባላስብም ልዩነትን የሚሰብኩ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደሉም፡፡ በየ ድረ ገጹ ሀይማኖትን መሰረት በማድረግ ጥፋትን የሚሰብኩ የድምጽና የቪዲዮ ምስሎች ለእልቂት የተላኩ ጊዜያቸውን ጠብቀው የሚፈነዱ ሚሳኤሎች ናቸው፡፡ በሜንጫ ጭፍጨፋን የሚሰብኩን የፖለቲካና የሀይማኖት ሰዎቻችንስ ከእኛው ጉያ የወጡ አይደሉምን!! መድረክ ሞቅ ባለጊዜ የሚናገሩትን የማያውቁ ሰዎች የራሳቸውን የውስጥ ጥላቻና ቂም በሀይማኖት ተቋሙ ስም የሚያደርጉት አንድ ሁለት ብሎ ከመቁጠር በላይ ተበራክተዋል፡፡
ያደገበትን እምነት ቀይሮ ወደ ሌላ የእምነት ተቋም በገባ ማግስት ከሚሄድበት ቤተ ጽሎት ከአመክንዮ ይልቅ የቀደመውን ቤቱን ሙልጭ አድርጎ የሚሰድብ ሰው ስንት ነው!! እምነት የግል ሆኖ ሳለ ‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል› እንዳለችው እኔ የሌለሁበት ቤት ባዶ ቀፎ ነው ብሎ መናገር ግብረ ገብነቱ የዜሮ ድምር ውጤት ነው፡፡
በዩንቨርሲቲዎች በየሀይማኖቱ ተቋማት የሚዘጋጁ የማጠናከሪያ ትምህርቶች አድሎ የበዛባቸውና የእበልጥ እበልጥ ፍክክር የሚታይባቸው ናቸው፡፡ ማጠናከሪያ ትምህርቱን የሚሰጠው መምህር አባል የሆነበት የእምነት ተቋም ውስጥ የሚማሩ ልጆች በዚያ የትምህርት ዓይነት ከሌላው እምነት አባል ከሆኑ ልጆች የላቀ ውጤት ያመጣሉ፡፡ አንዳንዴ እንዲያውም በመስጊድና አብያተ ክርስቲያናት ፈተናውን በውርክ ሽት መልክ የሚሰጡ መምህራኖችም ይገኛሉ አሊያም ቅሬታ የሚፈጠርባቸው ተማሪዎችም አሉ፡፡ 
1.4. አድርባይነት
አድርባይነት የሁሉም ሀይማኖት ተቋማት መለያ እየሆነ ነው፡፡ በተለይ በየጊዘው የሚመጡትን ገዥዎች ማወደስ ልማድ ነው፡፡ መጥፎም ይሁን ደግ መንግስት ዘመኑን ሲጨርስ በአንድ በሌላም ምክንያት ይቀየራል፡፡ ሀይማኖታዊ መጽሀፉ ግን የእግዚአብሄር ቃል ነው እና ያው ነው፡፡ በምንም መልኩ ዛሬ ያወደሰውን አገዛዝ የሚቀጥለው አመራር ሲመጣ ያለፈውን መኮነን ያለውን የማጽደቅ ስራ መሰራት አይችልም፡፡ የሀይማኖት ሰዎች ሁለት መልክ ሊኖራቸው አይገባም ነበር በመሰረቱ፡፡ በደርግ ዘመን ደርግን የደገፉ ደርግ ሲወድቅ ደርግን ጭራቅ ሰወ በላ ብለው ኢህአዴግን የሚቀድሱ የሀይማኖት ተቋማት ነው ያሉን፡፡ እርግጥ ነው ግለሰብ በአመለካከት ሊለያይ ይችላል ግን የግለሰቦች አስተያየት በተቋም ደረጃ ሲሆን አስቸጋሪ ነው፡፡
በክርስትናውም በእስልምናውም የሀይማኖት ያሉ መሪዎች ኢህአዴግ ሰልፍ ሲጠራ ሀይማኖታዊ ንዋየ ቅድሳትን ይዞ መውጣት የተለመደ ባህል ሆኗል፡፡ መንግስት ደግ ሲሰራ ይህን መንግስት ያኑርልን ብሎ መጸለይ ነውር አይደለም፡፡ ግን ደግሞ ሲሳሳትም መንቀፍ መለመድ ነበረበት፡፡ ዜጎች ሲፈናቀሉ፣ ያለስራቸው ለእስር፣ እንግልትና ሞት ሲዳረጉ፣ በእምነት ተቋማት አድኑኝ ብለው ሲጠለዩ አሳልፎ መስጠትና ማጨብጨብ ከምን የመጣ ነው!!
እኔ ሁሌ የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ አሁን በተለይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰላማዊ ሰልፍ መጥራት ከጀመሩ ወዲህ ኢህአዴግም እንዲሁ ማድረግ ጀመረ (ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ፓርዎች በፍጥነት የቀሰማት ምርጥ ተመክሮ)፡፡ ታዲያ ሀይማኖትን ወክለው በሰልፍ የሚገኙ የሀይማኖት አባቶች ጉዳይ ያሳስባል፡፡ የአንድ እምነት ምዕመን በሙሉ እንዴትም ቢሆን የአንድ ፓርቲ ደጋፊ ሊሆን አይችልም፡፡ እንኳን አሁን መንግስትና ሀይማኖት በህግ በተለዩበት ዘመን ቀርቶ በጃንሆይ ዘመንም ቢሆን ሁሉም ክርስቲያን ጃንሆይን ይደግፋል ማለት አይቻልም፡፡ ታዲያ የሀይማኖት ተቋምን ወክለው ሰልፍ የሚወጡ ሰዎች በምን ሂሳብ አደረጉት!! ቢሆንስ የአብያተ ክርስቲያናት ንዋዬ ቅድሳት ለምን የሰልፍ ማድመቂያ ይሆናሉ!! የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሄርን ለእግዚአብሄር እንዲል መጽሀፉ፡፡ ጥላውም ጸናጽሉም በስለት ያስገባው ይኸው ምዕመን ነውና፡፡ የገባው ደግሞ ለአምላክ ማወደሻ ልክብሩም መውረሻ እንጅ ኢህአዴግን ለማመገሻ አይመስለኝም፡፡ ይህ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡
1.5.  ጎሰኝነት
አንድ ወቅት ካርቱም መድሀኒዓለም ቤተክርስቲያን ሂጄ ይህን ታዘብኩ፡፡ በሱዳን ብዙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ከስደተኞቹም አንድ ዲያቆን አገኘውና ተጫወትን፡፡ ዲያቆኑ ካርቱም ከአንድ ዓመት በላይ ኖሯል፡፡ እንዲቀጥሩት ይፈልጋል- ግን የቤተ ክርስቲያኑ ቆሞስ ክፍተት ሲኖር ከአካባው ሰዎች በማስመጣት ብቻ እንዲቀጠሩ እንደሚያደርግ አጫወተኝ፡፡ አዘንኩ - አንደኛ በሚደረገው ሁለተኛም ልጁ አሳዘነኝ፡፡ ከዚሁ ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያውያኝ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት አለ፡፡ ቅጥሩ የሚፈጸመው ግን በተመሳሳይ እንዲሁ ከቀያቸው በሚመጡ ሰዎች ነው፡፡ ይህ በእውነት በክርስቶስ አንድ ነን እያሉ ለሚያስተምሩ ሰዎች በቤታቸው ይህ መኖሩ ያሳዝናል፡፡ እንደሚሰማው በምዕራብ ሀገራት ባሉ ብትን ወጎኖች /ዲያስጶራዎችም ይህ ነገር የገነነ ነው፡፡
አዲስ አበባ ያለ አንድን ደብር ማየት በቂ ነው፡፡ አስተዳዳሪው ከየት አካባቢ እንደሆነ ማየት ቀሪዎቹ አገልጋዮች የየት አገር ሰዎች እንደሆኑ መገመት አይከብድም፡፡ ክፍለ ሀገርም ወጣ ቢባል ከዚህ የተለየ አይሆንም፡፡ 
እንደ አጠቃላይ የእምነት ተቋማትን በዚሀ መልክ መጀመሪያ ማዬቴ የሞራል ቀዳሚ አስተማሪዎች ሆነው በሞራል እጦት ሲታመሱ ስመለከት ምዕመናኑ ሞራል የሌላቸው ቢሆኑ ብዙም የሚደንቅ አይደለም በማለት ይህን ጻፍኩ፡፡ የአሳ ግማቱ ከጭንቅላቱ ነው እንዲሉ፡፡ ክርስትና ሀይማኖትም ላይ ያተኮርኩት ከሌሎች የእምነት ተቋማት የተሻለ ስለማውቀው መሆኑ ይታወቅልኝ እንጅ ሌሎች ሀይማኖቶችም የዚህ ሰለባ አይደሉም ለማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ከምዕመን የማይጠበቅ ሀይማኖታዊ ዶግማና ቅኖና ተላልፌ ብገኝ የተሳሳትኩት በአለማወቅ እና በቅንነት እንጅ በድፍረት አሊያም በር ለመቅደድ ፈልጌ እንዳልሆነ በእግዚአብሄር ስም እናገራለሁ፡፡
በሚቀጥለው ሳምንት የዚህን ትውልድ እና የመንግስት ተቋማትን የሞራል ዝቅጠት ምን ያህል እንደከፋ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡  ይቀጥላል…….
መልካም አዲስ አመትና ሳምንት

1 አስተያየት: