ሐሙስ 6 ማርች 2014

የጎንደር ትኩሳቶች- የቅማንት የማንነት ጥያቄና የድንበር ውዝግብ


 
በከተማው መንፈሴን የሚይዝ ቦታ ፈለግኩ፡፡ ቋራ ሆቴል በረንዳ ላይ ተቀምጬ መጻፊያ ወረቀት ከፖርሳዬ አውጥቼ ቀና ስል ከኔ በላይ የሆኑ ቦታዎችን ተመለከትኩ፡፡ ስለሆነም ወደ ሰማዬ ሰማያት ትንሽ ጫማም ቢሆን ከፍ ማለት ሻትኩ፡፡ ባጃጅ ተኮናተርኩና ወደ ጎሃ ሆቴል በሶስት እግር ሮጥኩ፡፡ ጊዜው ከተሲያት ነው፡፡ ጎሃ ተራራ ላይ ተቀምጬ በሁሉም አቅጣጫ አማተርኩ፡፡ ከእኔ በታች አንዲት አሮጌ ከተማ አለች፡፡ በጣም ያረጀች፡፡ ስሟም ጎንደር የአጼ ፋሲለደስ መዲና፡፡
ከጎንድር ከተማ አናት ላይ ሆኜ ስለ ጎንደር መፍትሄ ስራይ ያልተገኘላቸው ትኩሳቶች እንዲህ እየጻፍኩ ነው፡፡ ጎንደር ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ለዬት ያሉ ሁለት አንገብጋቢ ትኩሳቶች ከፊቷ ተጋርጠውባታል፡፡ የቅማንት ብሄረሰብ የማንነትና ራስ አስተዳደር እንዲሁም የድምበር አከላል ጉዳይ፡፡ ሁለቱም እስካሁን መፍትሄ አልተሰጣቸውም፣ ሁለቱም ፍጹም ጡዘት ላይ ደረስዋል፡፡ ሁለቱም ታላቅ አገራዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡
የድንበር አከላሉ ሁለት መልክ አለው፡፡ አንደኛው ከትግራይ ክልል ጋር አጎራባች በሆኑ በአብርሃ ጅራ፣ አብደራፊና በአካባቢው ያለው ሲሆን በዚህ አካባቢ ያሉ ቀበሌዎችን ወደ ትግራይ ክልል ለመደባለቅ በሚደረገው እንቅስቃሴ ተፈናቀልን ያሉ የሰሊጥ አምራች ገበሬዎች እና ኢንቨሰተሮች ችግር አለ፡፡ ይህ ችግር አይደለም ባይባልም አገር እስካለች ድረስ ከሁለተኛው የድንበር ችግር አንጻር አንገብጋቢ ላይሆን ይችላል፡፡
ከባዱ የኢትዮ ሱዳን የድንበር ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ብዙ ፓለቲከኞችና ጸሀፍት ኢህአዴግ ‹አያደርገውም› ‹ያደርገዋል› እያሉ ሁለት የተለያዩ መላ ምቶችን ሲያስቀምጡ ሰነባብተዋል፡፡ ምንም እንኳ ጉዳዩን ኢህአዴግ እና ጊዜ የሚፈቱት ቢሆንም ኢህአዴግ ድምበሩን አሳልፎ ለሱዳን አይሰጥም የሚል ግምት የለኝም፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ በ1969 አካባቢ የዚያድ ባሬ መንግስት የምስራቅ ኢትዮጵያን እስከ ድሬ ደዋ ድረስ በእብሪት ሲወር የሶማሊያን አቋም በመደገፍ የኢትዮጵያ መሬት ስላልሆነ ወረራው አግባብነት አለው በማለት ከባዕድ መንግስት ጎን መቆሙን የፖለቲካው እስረኛ አንዷለም አራጌ ‹ያልተኬደበት መንገድ› በሚለው መጽሀፉ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በዚህ እሳቤ የአሁኑ መሬትም በሰሜን ምዕራብ መገኘቱ ካልሆነ በስተቀር ምንም ልዩነት ስለሌለው ‹መሬቱ የሱዳን መንግስትና ህዝብ ነው› ብሎ ሊያስረክብ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ምናልባት የሚረከብበት ጊዜና የሚረከበው መሬት ነው በውል ያልታወቀው፡፡ (የሚወራውን ያክል መሬት ለባዕድ ተላልፎ ከተሰጠ ግን የሚያሳዝነው እነ አጼ ቴዎድሮስ የተወለዱበትን እና የሸፈቱበትን ቦታ እንዲሁም አጼ ዮሀንስ በመሀዲሰት ጦር አንገታቸውን የተቆረጠበትን ቦታ ለመጎብኘት የሱዳን ፓስፖርት ማገኘት ግድ የሚለን ጊዜ ሲመጣ ማዬት ነው፡፡ መሀዲስቶችም ጎንደርን ካቃጠሉ ከ120 ዓመት በኋላ መልሰው ጎንደር ወሰዱ ማለት ነው፡፡ ጣሊያን ከ40 ዓመት በኋላ መጥቶ እንደተሳካለት ሁሉ!!)
የድንበሩን ጉዳይ ገታ እናድርግና ወደ ሌላኛው የጎንደር ትኩሳት እንለፍ፡፡ የቅማንት ብሄረሰብ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ሌላው አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ አገኝቸዋለሁ፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት አባ ወንበሩ መርሻን ጭልጋ ወረዳ ገጠር ድረስ ሂጄ አነጋግሬያቸዋለሁ፡፡
የቅማንት ህዝብ ከአገው ህዝቦች እንዳንዱ የሚቆጥሩት አሉ፡፡ አገዎች በኤርትሪያ (ብሌን)፣ በወሎ (ዋግኸምራ)፣ በጎንደር (ቅማንት) እንዲሁም በጎጃም (አዊ) ይኖራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ያሉት አገዎች ከቅማንት ውጭ ሁሉም ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድራሉ፡፡
የቅማንት ህዝብ በብዛትና አልፎ አልፎም ቢሆን በጭልጋ፣ በጎንደር ዙሪያ፣ በደንቢያ፣ በደጋው ቋራ፣ በላይ አርማጭሆና በመተማ ይኖራል፡፡ ቋንቋው በመጥፋት ላይ ቢሆንም የሚናገሩ በእድሜ ገፋ ያሉ ሰዎችን አግኝቻለሁ፡፡ አብዛኛው (ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል) ህዝብ የኦርቶዶክስ ክርስትና አማኝ ነው፡፡ ክርስትናቸው የቅርብ ጊዜ መሆኑንና ቀደም ሲል ወደ ኦሪት እምነት የቀረበ እንደነበር አባወንበሩ ይናገራሉ፡፡ ‹ወንበር› በቅማንት እምነት የመጨረሻው የተከበረ ሰው ማዕረግ ነው፡፡ ስለሆነም ‹ቅማንት› የሚለው የሀይማኖትም፣ የቋንቋም፣ የባህልም መገለጫ ነበር፡፡ አሁን አሁን ቅማንት የማንነትና የቋንቋ መገለጫ ይሆን እንደሆን እንጅ የሐይማኖት ሊሆን የሚችል አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ነበሩን እምነት የሚከተሉ ሰዎች በቁጥር እጅግ በጣም አናሳ ናቸው፡፡ የአባ ወንበሩም ልጆች ሳይቀር ክርስትያን መሆናቸውን ነገረውኛል፡፡
በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 39/5 ላይ አንድ ህዝብ በተያያዘ መልክዓ ምድር ሆኖ አንድ አይነት ታሪካዊ አመጣጥ ካለው፣ የስነ ልቦናና የራሱ የሆነ መገለጫ ካለው ራሱን በራሱ ሊያስተዳድር እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ በዚህ እሳቤ እንደኔ እምነት የቅማንት ህዝብ ማንነቱ እንዳይታወቅ የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ የህዝቡን ቋንቋና ባህል መጠበቅ ሀገራዊ ሀብት ይመስለኛል፡፡
ሆኖም ግን እስካሁን መፍትሄ ሳይሰጠው መቆዬቱ የተወሳሰቡ ችግሮችን እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ችግሩን ያወሳሰበው ደግሞ የህወሓት/ኢህአዴግ ሁለት መልክነት ይመስላል፡፡ ኢህአዴግ እንደ ‹አማራ› እና ‹እንደ ህወሓት› ዓይነት ሁለት መልኮችን ለብሶ የቅማንትን ህዝብ ችግር በጣም አወሳስቦታል፡፡ ይህም ሌላው ‹ለአማራ ህዝብ የተቀበረ ፈንጅ› አድርጎታል፡፡ ይህን በተጨባጭ አመክንዮ እንመልከት፡፡
በሁለተኛው የህዝብ ቆጠራ በ1984 ዓ.ም. በተገረገው የቅማንት ህዝብ ወደ 172000 አካባቢ የነበረ ሲሆን በ1999 ዓ.ም. ደግሞ ቅማንት የሚለውን ማንነት ሰርዞ ‹አማራ› በሚል ሰር እንዲቆጠሩ አደረገ፡፡ ይህ የመጀመሪያው ሴራ ነው፡፡ ከዚያም ይህን የኢህአዴግ ሳይሆን ‹የትህምከተኛ› አማሮች ሀሳብ መሆኑን እራሱ ህወሓት በሚያንቀሳቅሳቸው ደረ ገጾች እንዲቀጣጠል አደረገ፡፡ በፈረንጆች አቀጣጠር በጁላይ 12 ቀን 2013 አንድ በብዕር ስሙ ምዝገና አደራ የተባለ ሰው “Unfinished Amharization Process in Ethiopia and Qimants Quest for Dignity and Self Rule” በሚል ርዕስ በtigraionline.com ባስነበበው ጽሁፍ የአማራን ህዝብ ሲከስ ‹‹በሚኒሊክ የተጀመረው ህዝብን በግዳጅ አማራ የማድረግ ሂደት እስካሁን አልተቋጨም፡፡ አሁንም በግዳጅ ሰዎችን የአማራ ህዝብን ቋንቋና ባህል እንዲቀበሉ በማስገደድ በአማራ መንግስት እንዲተዳደሩ ማድረጉ እንደቀጠለ ነው፡፡ ... የአማራ ፈላጭ ቆራጮች አሮጋንት አማራዎችን በያዘው በካንጋሮ ፓርላማቸው እያስቀጠሉት ነው፡፡ ሆኖም ግን የማንነታችን ጥያቄ መልስ እስከሚያገኝ እንዲሁም ከአማራ ቅኝ ግዛት እስክንወጣ ማንኛውንም አይነት የትግል ስልት እንጠቀማለን፡፡›› (የተሰመረበት ከራሴ)
ምናልባትም ይህን የጻፈው አንድ የህወሓት ጀሌ ሊሆን ይችላል ብዬ አስቤ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም አንድ ባለ 100 ገጽ ‹የቅማንት ህዝብ የማንነት ጥያቄ እና የኢፈድሪ ህገመንግስት› የሚል አሁንም በብዕር ስሙ ትንቢቱ ደረሰ የሚባል ሰው የጻፈውን መጽሀፍ ሳነብ ተመሳሳይ መልዕክት ያለውና በተለይ ‹አማራውን› ሙልጭ አድርጎ እንደ ሰሞኑ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ተብዬ የሚሰድብ ሆኖ አገኝቸዋለሁ፡፡
ሌላው የቅማንት ብሄረሰብ የማንነት እና የራስ አስተዳደር ይፈቀድልኝ አስተባበሪ ኮሚቴ በ1999 ዓ.ም. ከተቋቋመ በኋላ በተከታታይ ለክልሉ መንግስት እንዲቀርብ ተደረገ፡፡ በ2003 ዓ.ም. በክልሉ መንግስት ጥናት ተደርጎ ከ6645 በላይ ቋንቋውን ተናጋሪ ሰዎች ቢገኙም ቋንቋው እንደሞተ በመቁጠር ሰላማዊ ሰልፍ እንኳ እንዳይወጡ እስከዚህ ዓመት ድረስ እንዲቆዩ ሆነ፡፡

ስለ ብሄረሰቡ መኖር በርከት ያሉ ሰዎች ጥናትና ምርምር አድረገዋል፡፡ በጎንደር ዩንቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፐሮፌሰር ይግዛው ከበደም ተመሳሳይ ጥናት አቅርበዋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም የብሄረሰቡን መኖር የሚያረጋግጡ ጥናቶች ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ተደርጓል፡፡ ይህም አስተባባሪ ከሚቴዎችንና አንዳንድ የህብረተሰቡን ህልውና መኖር የሚፈልጉ ወገኖችን በእጅጉ አስቆጥቶ በአማራ ህዝብ ላይ በጥላቻ እንዲነሱ አደረገ፡፡
በሳለፍነው ሳምንት እሁድ የካቲት 2006 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ በተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ ሁለት ተቃራኒ ሀሳቦች ተንጸባርቀዋል፡፡ አንደኛው ህወሓት/ኢህአዴግን መደገፍ ሲሆን ‹አማራ ኢህአዴግን› ደግሞ መቃወም ነው፡፡ የክልሉን መንግስትና ህዝብ እንቃወማለን የሚሉ ወገኖች በሌላ በኩል የመለስን ፎቶ ግራፍ በመያዝ ‹‹የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ራዕይ እናስፈጽማለን›› የሚለ መፈክሮች ይሰሙ ነበር፡፡ (በጊዜው በጎንደር አቢዮት አደባባይ ከ20-30 ሺህ የሚገመት ሰው ለሰልፉ ከተለያዩ ወረዳዎች ወጥቶ ነበር፡፡)
አሁን የኢህአዴግ ሁለት ገጽታነት በጉልህ የታዬ ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ ‹በአማራነቱ› ቅማንትን ማጥፋትና አስገድዶ አማራ ማድረግ፣ ሰላማዊ ሰለፍ መከልከል ሲሆን በ‹ህወሓትነቱ› ደግሞ የተከለከሉበትን ምክንያት ከአማራው ህዝብ አሮጋንትነት ምክንያት ነው በማለት ድረ ገጾችን በማመቻችት የጥላቻ መርዝ መዝራት ነው፡፡
የቅማንት ብሄረሰብ የማንነት ጥያቄ የመጨረሻ ጡዘት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አሁን ህወሓት/ኢህአዴግ የሚፈልገውን ራዕይ ለማሳካት የበቀሉ ፍሬ ሲያፈራ ማዬት ብቻ ይሆናል፡፡
ጥያቄ አቅራቢዎቹ በሰሜን ጎንደር ባሉ ስምንት ወረዳዎች (ጎንደር ከተማን ጨምሮ ወገራን፣ ላይ አርማጭሆን፣ ጎንደር ዙሪያን፣ደንቢያን፣ ጭልጋን፣ ቋራንና መተማን) 126 ቀበሌዎችን በልዩ ዞኑ እንዲካተቱ እና ጎንደር ከተማ አዲስ የሚመሰረተው የቅማንት ልዩ ዞን ከተማ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ ምንም እንኳ ማረጋገጥ ባልችልም ጎንደር ከተማ ሁለት ከተማ አስተዳደር እንዲሆን ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ አዘዞ ከተማ አስተዳደርና ጎንደር በሚሉ፡፡ እንደሚባለው ከሆነ አንደኛው ከተማ ለልዩ ዞኑ ከተማነት ያገለግላል፡፡
እንደ መውጫ
የቅማንት ብሄረሰብ የማንነት ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ነገር ግን የሁሉንም ህዝብ ፍላጎት ያገናዘበ መሆን ይኖርበታል፡፡ ተወደደም ተጠላም አንዳንድ ጉዳዩን የያዙ ሰዎች ሕወሓቶችን የሙጥኝ ቢሉም ቅሉ ለቅማንት ህዝብ በአካባቢው ያለው የተዋለደውና የተዛመደው ጎንደሬ እንጅ ሌላው የሚቀርበው አይመስለኝም፡፡  
ሌላው የብሄረሰቡ ልዩ ዞን በሚካለልበት ጊዜ የአብዛኛውንም ህዝብ መብት በሚረግጥ መልኩ መሆን እንደሌለበት መንግስት ሊያስብበት ይገባል፡፡ ጭልጋ ወረዳ ላይ አብዛኛው ቅማንት ቢሆን ወገራ ላይ አሊያም ደንቢያ ላይ ትንሽ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም የብዙሀኑን ጥያቄም ግንዛቤ ያስገባ መሆን አለበት፡፡ የጎንደር ከተማ እጣፈንታም አስቸጋሪ ይመስላል፡፡ እንደ ማዕከላዊ እስታስቲክ ከሆነ የጎንደር ከተማ ህዝብ ከ85 ፐርሰት በላይ የአማራ ህዝብ ያለበት ከተማ ነው፡፡ ከ6 ፐርሰንት በላይ የሚሆነው ደግሞ የትግራይ ብሄረሰብ ነዋሪ ነው፡፡ ስለሆነም የ85 ፕረሰንቱን ህዝብ ፍላጎት ጥሶ የሚጸድቅ ከሆነ አስቸጋሪነቱ ብዙ መልክ ይኖረዋል፡፡
ማንነት ክብር ነው፡፡ ማንነትን ለማግኘት ግን የሌላውን ማንነትም መረገጥ አደጋ አለው፡፡
ሰላም፡፡

3 አስተያየቶች:

  1. ውድ ወንድሜ ሙሉቀን ተስፋው ገለልተኛ ለመሆን በመመከር የፃፍከው ፅሁፍ እጅግ በጣም ተመችቶኛል፡፡ ሥለ ቅማንት በራሱ ደፍሮ መፃፍ የሚያኮራና በጀ የሚያስብልህ ነው፡፡ ግርም የሚለኝ ድረ ገፅ ላይ ፈላሻ ብለህ ብትገባ በጣም ብዙ ነገር ታነባለህ፡፡ ቅማንት ብለህ ብትገባ ግን ምንም አታነብም፡፡ ከፈላሻ እኛ እንበዛለን የሚገርመው ግን አማራነት ውጦናል፡፡ እንደሚታወቀው ባብዛኛው ከተሞች አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎችም የክልል ከተሞች ሳይቀር የሚኖረው ነዋሪ አማራ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የጎንደርም ተመሳሳይ እንደሆነ አምናለሁ፣ ግን ከተማ ላይ በሚኖረው አማራ ተወስኖ ከተሞች ከገጠሩ ተለይተው ልዩ ዞን ሲሆኑ አላየሁም፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ፣ ናዝሬት፣ አሰላ፣ ድሬዳዋ፣ አለማያ፣ አሶሳ፣ ቻግኒ፣ ጋምቤላ፣……. እኒህ ከተሞች ግን የአማራ ልዩ ከተሞች እንደማይባሉ የታወቀ ነው፡፡

    እኔ ቅማንት ነኝ፣ ነገር ግን ባህር ዳር መታወቂያ ሳወጣ ቅማንት የሚባል የለም አማራ ነህ ብለው በኣማራ ነው የተሠራልኝ፡፡ ጎንደርስ እንዲህ እንደኔ የሆነው ስንቱ ይታወቃል ብለህ አስበኸዋል? ድሮ አማራ መባል ድንቅ ነበር አሁን ግን ያስቀጠቅጣል፣ ካማራ ጋር የሚደረጉ ግጭቶች ገፈት ቀማሽ መሆን ምርር ብሎናል፡፡ ሥለዚህ ቅማንት መባልን ነው የምንመርጠው፡፡ አንተ ጎንደር የቅማንት ከተማ ብትሆን ቅር የሚትሠኝ ትመስላለህ፣ ግን ጎንደር ራሷ ብትጠየቅ ደስታውን የምትችለው አይመስለኝም፡፡ ምክኒያቱም የቅማንት ከተማ በመሆኗ ከተማነቷ ቢጨምር እንጂ ትጎሳቆላለች የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሕዝቡም ቅር የሚለው አይመስለኝም፡፡ ደግሞም እኮ አንተ እንዳልከው የተዛመድን አንድ ሕዝቦች ነን፡፡

    ሌላው ግን ግርም የሚለኝ እንዲያው ያንተ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ችግር የሕዝብ ቁጥርን በተመለከተ ነው፡፡ ሠልፍ ላይ የሚወጣ ሕዝብና የሚነገረው የህዝብ ቁጥር ይደንቀኛል፡፡ መዓከላዊ ስታቲስቲክስ የጎንደር ሕዝብ ቁጥር ሁለት መቶ ሽህ እንደሆነ ይገልፃል፤ አንዳንድ ፅሁፎች ላይ እንዳነበብኩት ከሁለት እስከ ሶስት መቶ ሽህ ህዝብ ለሰልፉ እንደወጣ ነው፡፡ አንተም በተመሳሳይ ከሃያ እስከ ሰላሳ ሽህ የሚሆን እንደታደመ ገልፀሃል፡፡ በሌላው ሃሳብህ ደግሞ 85 መቶኛው አማራ 6 መቶኛው ትግሬ እንደሆነ አሳምነህናል፡፡ ሠልፉ ላይ የወጣው ሕዝብ አንተ ያልከው ቢሆን እንኳን 15 በመቶው የጎንደር ሕዝብ ቅማንት ሆነ ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ የሚወራረድ ሒሳብ ያለ ይመስለኛል፡፡ 91 መቶኛው አማራና ትግሬ ከሆነ ሌላው 9 መቶኛው (የቅማንት ቁጥር አይታወቅም ከአማራ ጋር ተደርቦ ስለሚቆጠር) ሌላ ሌላ ብሔረሠብ ሆነ ማለት ነው፡፡ አኔ ደግሞ አንተ ያልከኝን ይዠ እንድ እንኳን ከህፃን እስካዋቂ ሁሉም ቅማንት እንደወጣ አስቤ፤ አንተ ባመንከው ከጎንደር ሕዝብ 15 መቶኛ የቅማንት ቁጥር አገኘሁ፡፡

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  2. Thank you both( the writer and the commenter ) i have no any information about the community as they are exist now,therefore,they should develop their culture,language and all things related with them.They should not dominate by any one.I think the same case is exist in the southern part of Ethiopia.Many Thanks!

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  3. kimant malet ageru gonder kimal yemibela kimal yalebet malet new kimalam

    ምላሽ ይስጡሰርዝ