2014 ጁን 1, እሑድ

እናቱ መፀዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ የከተተችው ህፃን ከሞት ተረፈ በሐረር ከተማ “ማሳደግ አልችልም” በሚል ሰበብ የወለደችውን ህፃን በፌስታል አድርጋ መፀዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ የከተተች እናት በቁጥጥር ስር የዋለች ሲሆን ህፃኑ ከ6 ሰዓት በኋላ ከጉድጓዲ ወጥቶ ህይወቱ ተርፏል፡፡ በሐረሪ ክልል በቀበሌ 19 ልዩ ስሙ አማሪሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆነችው የ20 ዓመቷ ወጣት፤ ባለፈው ሐሙስ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ የተገላገለችውን ህፃን በፌስታል አድርጋ መፀዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ እንደከተተችው የክልሉ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮማንደር ጣሰው ቻለው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ ወደ ሽንት ቤት ያመራ ጎረቤት የህፃኑን ለቅሶ ሰምቶ ለፖሊስ መጠቆሙንና ህፃኑ በመፀዳጃ ቤቱ ጉድጓድ ውስጥ ተንሳፎ በህይወት መገኘቱን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገልፀዋል፡፡ በቀን ሥራ የምትተዳደረው እናት ቤቷ ውስጥ ተኝታ መገኘቷን የገለፀው ፖሊስ፤ ህፃኑን መፀዳጃ ቤት ውስጥ የከተተችው የማሳደግ አቅም ስለሌላት እንደሆነ በመናገር ድርጊቱን መፈፀሟን አምናለች ብሏል፡፡ህፃኑ በሐረር ከተማ በሚገኘው የህይወት ፋና ሆስፒታል በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ፖሊስ ጠቁሞ፤ እናትየው ምርመራ እየተደረገባት እንደሆነ ገልጿል፡፡ (Source Addis Adimas news paper)

2014 ኤፕሪል 7, ሰኞ

ሰበር ዜና- በጎንደር ከተማ የ3 ሽህ ሰዎች መኖሪያ ቤት ይፈርሳል!!

በጎንደር ከተማ በህገ ወጥ መልኩ ተገንብተዋል የተባሉ ከ3 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች ሊፈርሱ ነው፡፡ ቤቶቹ በተለምዶ የጨረቃ ቤት ናቸው በሚል ሰበብ የሚፈርሱ ሲሆን እንደ አንዳንድ አስተያዬት ሰጪዎች የቤቶቹ መፍረስ የቤት አልባ ሰዎችን ቁጥር ከፍ እንደሚያደርገው ያምናሉ፡፡ ብዙ ቤተሰቦችም እንደሚፈናቀሉ ይታመናል!! መንግስት ቤቶቻቸው የሚፈርስባቸውን ቤተሰቦች ችግር ከወዲሁ ሊያጤነው እንደሚገባ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡

2014 ማርች 24, ሰኞ

አማላጅ ያልተገኘለት የኢትዮ ቴሌ ኮም ጉዳይ - Disconnecting the Future


ስሙን እና አርማውን ብቻ ቀይሮ በግብር ግን ወደ ኋላ እየተንቀሳቀሰ ያለ ተቋም እንደ ኢትዮቴሌኮም አይገኝም፡፡ አንድ ጊዜ የፈረንሳይ ሌላ ጊዜ ደግሞ የቻይና ኩባንያወዎች እየተፈራረቁበት የሚገኘው ኢትዮቴሌኮም አሁን አሁን በተለይም ከቅርብ ወራት ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ነው ማለት የሚከብድ ይመስለኛል (ምናልባትም ከስለላ ስራው ውጭ)፡፡ በአፍሪካ አነስተኛ ደንበኞችን በብቸኝነት ይዞ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የተሳነው አንጋፋው ድርጅት ነው፡፡ በእድሜ ብዛት ለውጥ አቅቶታል፡፡ ጎረቤት አገራት በርካታ የቴሌ ኩባንያዎች አላቸው፡፡ ሱዳን ውስጥ ከአራት በላይ አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማት አሉ፡፡ ሱዳኒ፣ አረቢ፣ ኤም ቲ ኤን ... ይጠቀሳሉ፡፡ በጸጥታው ዘርፍ እንኳ እየታመሰች ያለችው ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ሶምቴል፣ ቴሌሶም፣ ቴሌኮም፣ ኤም ቲ ኤን የሚባሉ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አሏቸው፡፡ ከኬንያ ጋር መወዳደር አይቻልም፡፡ ታዲያ ምንም አማራጭ በሌለበት ሁኔታ ይህ ተቋም ከዘመድ አዝማድ ሁሉ ሊያቆራርጠን ነው፡፡ ከሚያውቁት ሰው ሲደውሉ የማያውቁት ሰው ያነሰዋል፡፡ ይቅርታ ጠይቀው እንደገና ያንኑ ቁጥር ሲመቱት በመካከል ሙዚቃ ይገባብዎታል፡፡ ሙዚቃው እስኪጨርስ ከጠበቁት በራሱ ጊዜ ይዘገዋል፡፡ አሁንም ሌላ ዘመድዎ ጋር ቢደውሉ ጆሮ የሚያደነቁር ድምጽ ሊሰሙ ይችላሉ፡፡ ሌላ ሰው ጋ ሳይሰለቹ ከደወሉ ከብዙ ሙከራ በኋላ ‹‹ይቅርታ የደወሉለትን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም›› የሚል ሰቅጣጭ ድምጽ ይሰማሉ፡፡ የዚች ሴቲዮ ድምጽ በስልክዎ ሲያሰለችዎት ስልክዎን ሊወረዉሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ መካከል ሁለት ነገሮች ያልቃሉ፡፡ አንደኛው ገንዘብዎት ምንም ሳያወሩ ያልቃል፡፡ ሁለተኛው የሞባይሉ ባትሪ እንዲሁ ያልቃል፡፡ የኢትዮጵያ መብራት ሀይል እርሱም መብራቱን አጥፍቶት ከሆነ ለቀናት የተዘጋ ሞባይል ቀፎ ይዞ ለመዞር እንገደዳለን፡፡ እናም በዚህ አካሄድ በ2020 ኢትዮጵያውያንን ከዓለም ጋር ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያውያን ጋር የሚቆራርጠን ይሆናል፡፡ አይበልብንና ሌባ ቢመጣ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከመደወል ሰወው መላክ ይቀላል፡፡ ስልክ እስኪደወል ወንበዴው የፈለገውን ማድረግ ይችላል፡፡ አማልዱን ብለን አማለጅ አንልክ በማን እንሂድበት!! የጃን ሆይን ሞዓ አንበሳ አርማ አስወግዶ ኔትወርኩንም ኖት ዎርክ (Network to Not-work) አደረጎት አረፈ፡፡ እንደባለፉት ዘመናት ሁሉ በፖስታ በኩል መላላክ ብቸኛው አማራጭ ሊሆን ነው፡፡ የፖስታ ቤት ባለስልጣን ማርኬቲንግ ክፍል አስቦበት ከሆነ በርከት ያሉ የፖስታ ቁጥሮችን እንዲሁም ቅርንጫፎቹን ማብዛት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ቴሌኮም እንደሆን ከቀን ቀን እየሆነ ያለውን እያየነው ነው፡፡

2014 ማርች 22, ቅዳሜ

ሰበር ዜና – የማኅበረ ቅዱሳንን አመራርና አባላት በአክራሪነት የሚከስ ዶክመንተሪ ሊዘጋጅ ነው ተባለ


ዶክመንተሪው የ2007 ሀገራዊ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት አካል እንደኾነ ተጠቁሟል ‹‹ማስረጃ አቅርቡና እንነጋገርበት›› ለሚለው የማኅበሩ ጥያቄ ምላሽ አልተሰጠም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሲኖዶሱን ይኹንታ አግኝቶ በመላው አገሪቱ የሚንቀሳቀሰውን የማኅበረ ቅዱሳንን አመራርና አባላት በአክራሪነት የሚከስ ነው የተባለ ዶክመንተሪ ፊልም ለማዘጋጀት መታቀዱ ተጠቆመ፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አንዳንድ ሓላፊዎች አቀብለውታል በተባለ መረጃ እንደሚታገዝና በመንግሥት አካል እንደሚሰናዳ የተገለጸው የዶክመንተሪ ዝግጅቱ በማኅበሩ ኻያ አመራሮች እና አባላት ላይ እንዳነጣጠረ ተገልጧል፡፡ መንግሥት በምርጫ – 97 ውጤትና በተከታይ ኹኔታዎቹ ላይ ባካሔደው ግምገማ፣ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ናቸው የሚባሉ ግለሰቦች በተለይ በገጠር ቀበሌዎች ለተቃዋሚዎች ተሰሚነት ማግኘት በምክንያትነት መጥቀሱ በዜና ጥቆማው የተመለከተ ሲኾን ‹‹የአክራሪነትና የጽንፈኛ ፖሊቲከኞች ምሽግ ነው›› በሚል የሚያቀርበው ክሥም ከዚኹ የሚነሣና ለመጪው የ2007 ሀገራዊ ምርጫ የሚደረግ ቅድመ ዝግጅትም አካል እንደኾነ ተነግሯል፡፡ በቅድመ ዝግጅቱ የሚወሰዱ ርምጃዎች የማኅበሩን አቅሞችና እንቅስቃሴዎች በመቆጣጠር በተለይም የማኅበሩ መሠረቶች ናቸው የሚባሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያትን ‹‹በሴኩላሪዝም መርሖዎች የመግባቢያ ሰነድ›› ጠርንፎ ‹የአገልግሎት ቅኝቱን የማስተካከል› ዓላማ እንዳላቸው የገለጸው የዜና ምንጩ፣ ይህም ካልተሳካ በተከታታይ አስተዳደራዊ ርምጃዎችና የተቃውሞ ቅስቀሳዎች ማኅበሩን በማወከብ ተቋሙን ለዘለቄታው የማፍረስ ውጤት ሊኖረውም እንደሚችል አመልክቷል፡፡ ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አብያተ ክርስቲያናት የተጠሩ ናቸው የተባሉ አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች የሚሳተፉበት እንደኾነ የተገለጸና ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በማኅበሩ አገልግሎት ላይ ቁጥጥሩን እንዲያጠብቅ የሚጠይቅ ስብሰባ በዛሬው ዕለት በቤተ ክህነቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንደሚካሔድ የተዘገበ ሲኾን ዓላማውም ‹‹በአክራሪዎችና ጽንፈኛ ፖሊቲከኞች ምሽግነት፣ የቤተ ክህነቱን አሠራር ባለማክበርና ከቤተ ክህነቱ በላይ ገዝፎ በመውጣት›› ማኅበሩ የሚከሰስባቸውን ኹኔታዎች በማጠናከር ለታቀዱት ርምጃዎች የሚያመቻች ነው ተብሏል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ላይ በማተኮር የተማረው ትውልድ ሃይማኖቱን የሚወድ፣ ግብረ ገብነት ያለው፣ ሀገሩንና ቤተ ክርስቲያኑን በዕውቀቱ፣ በሞያውና በገንዘቡ የሚያገለግል ብቁ ዜጋ ይኾን ዘንድ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደርያ ደንብ መሠረት በመሥራት ላይ እንዳለ የሚገልጹ የማኅበሩ አባላትና ደጋፊዎቹ፣ ማኅበሩ ለቀረቡበት ክሦች የሚመች አደረጃጀት ይኹን ባሕርይ እንደሌለው በመግለጽ ተጠሪ ከኾነለት ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋራ በአሠራር ሒደት የሚፈጠር ክፍተትን በማጦዝ የሚሰነዘሩ ውንጀላዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ የተጠቀሱት ክሦች ላቀረቡት አካላት ‹‹የሚነገረውና የሚጻፈው እኛን የሚገልጸን ስላልኾነ ማስረጃ አቅርቡና እንነጋገርበት›› የሚል ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ለሠለጠነ ውይይት ፍላጎት እንደሌላቸው አባላቱ አስረድተዋል፤ በምትኩ ‹‹ርምጃ እንወስዳለን›› በማለት በተለያዩ መድረኮች ማኅበሩን ማሳጣትና መክሠሥ እንደሚመርጡም ለፋክት መጽሔት አስታውቀዋል፡፡ ታቅዷል የተባለው የዶኩመንተሪ ዝግጅት እውነት ከኾነም ማኅበሩን ብቻ ሳይኾን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የማዳከም አጠቃላይ ዘመቻ አድርገው እንደሚቆጥሩትና በቀላሉ እንደማይመለከቱት አሳስበዋል፡፡ sources:(ፋክት፤ ቅጽ ፪ ቁጥር ፴፰፤ መጋቢት ፳፻፮ ዓ.ም.)

2014 ማርች 13, ሐሙስ

በሸንቁጥ አየለ የተደረሰዉ ኅቡእ ጣት (ዘ ሀይድ) መጽሀፍ ዕሁድ መጋቢት 7/2006 ዓም በሀገር ፍቅር ቲያትር ይመረቃል በሸንቁጥ አየለ የተደረሰዉ ኅቡእ ጣት (ዘ ሀይድ) መጽሀፍ ዕሁድ መጋቢት 7/2006 ዓም በሀገር ፍቅር ቲያትር ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ይመረቃል:: በምርቃት ፕሮግራሙ ላይ ታዋቂ ሰዎች : ጋዜጠኞችና የስነ ጽሁፍ ባለሞያዎች ተገኝተዉ ስለ መጽሃፉ ያላቸዉን አስተያዬት ይሰጣሉ:: ኅቡእ ጣት (ዘ ሀይድ) መጽሀፍ ኢትዮጵያ በዉስጡዋና በዙሪያዋ ባሉ ልዩ ልዩ ስነልቦናዊ: ታሪካዊ : ፖለቲካዊ: ሳይንሳዊና ማህበራዊ ጭብጦች ዙሪያ የሚያጠነጥን መሆኑ ተገልጾአል:: ዙሪያዋን ያሉ ታላላቅ የሀገሪቱ ጠላቶች ኢትዮጵያ ፈርሳ ማዬት ትልቁ የቤት ስራቸዉ ብቻ ሳይሆን ከፍ ያለ ቅዱስ ተልዕኮአቸዉም መሆኑን የሚተርከዉ ይህ መጽሀፍ የሚያጠነጥነዉ የሀገሪቱ ባላንጣዎች ታላቁን የቤት ስራቸዉን ብሎም ቅዱስ ተልዕኮአቸዉን ለማሳካት በታላቅ ትጋት : በከፍተኛ ጥበብና በሙሉ ሀይላቸዉ ስራቸዉን ሲከዉኑ ያሳያል ተብሎአል:: ሀገሩ ያበሳቆለችዉንና የገፋችዉን ተራ ዜጎች ብሎም መንግስት ጆሮ አልስጥ ያላቸዉን ታታላቅ ሳይንቲስቶችን ጭምር ለዚህ ተልዕኮ ሊያሰልፉዋቸዉ ሲባትቱ የሚከተሉዋቸዉን ሂደቶች ልብ ሰቃይ በሆነ መልክ ያሳያል:: ይህ መጽሀፍ ሳይንስ በኢትዮጵያ ምድር ፍሬ እንዲያፈራ ከተፈለገ ባለ አዕምሮ የሀገሪቱ ዜጎች የሚሉትን በጥንቃቄ ማድመጥ ወሳኝ መሆኑን ለማሳዬት እንደሚሞክር ተገልጾአል:: የሀገሪቱ ብሄሮች ወደ ከፍተኛ ቅራኔና የእርስ በእርስ መጠፋፋት እንዲገቡ በመጨረሻም ሀገሪቱ ፍርስርሱዋ እንዲወጣ ሁሉንም አሉታዊ ድሮች የሚያደሩት የሀገሪቱ ባላንጣዎች ብርና ሀብታቸዉን በኢትዮጵያ ምድር እንደ ጉድ ሲያፈሱት የሚያሳይ ብሎም ስለላ : ንግድ እና ሸፍጥ ተጎናጉነዉ ሲጦፉ የሚተርክ መጽሀፍ መሆኑን ደራሲ ሸንቁጥ አየለ አብራርቶአል:: ሀገር ከሰራዊት በላይም የዜጎቹዋ ጥበቃ የግድ ያስፈልጋታል በሚል ጽኑ መርህ ላይ የቆመ መልዕክት ያለዉ ይህ መጽሀፍ የግብጽና የሌሎች ጎረቤት ሀገራት ኢትዮጵያን የማፍረስ ተልዕኮ በኢትዮጵያዉያን ዜጎች እንዲከሽፍ ከተፈለገ ከብሄረተኝነት ይልቅ ኢትዮጵያዊነት ብቸኛ መሳሪያ ነዉ የሚል ጥልቅ ይዘትን እንደሚያስተላልፍ ታዉቁአል:: በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ባላት የዉሃ ሀብትና ሌሎችም ተያያዥ ሀብቶች ግብጽ ስታገሳ ኤርትራ ስትወናጨፍ ሌሎች ጠላቶች እያጨበጭቡ ኢትዮጵያ ያላትን ሁሉ ሊያሳጡዋት ቢዘጋጁም ኮሳሶቹ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ግን ኢትዮያዊነትን እንደ ኒኩሊየር አረር ሲተፉ የሚተርክ መጽሀፍ መሆኑ ታዉቆአል:: 206 ገጽ ያለዉ ኅቡእ ጣት (ዘ ሀይድ) መጽሀፍ የሸንቁጥ አየለ ሁለተኛ የመጽሀፍ ስራዉ ሲሆን ከዚህ በፊት የጠፍ ከዋክብት የሚል መጽሀፍ ማሳተሙም ታዉቁዋል:: ደራሲዉ ከዚህ በተጫማሪም ማዕበል የሚል ፊልም ደርሶ ለህዝብ ማቅረቡና ልዩ ልዩ ጽሁፎችን በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ለአንባቢያን የሚያቀርብ መሆኑ ተገልጾአል:: ኅቡእ ጣት (ዘ ሀይድ) መጽሀፍ ከመጋቢት 7/2006 ዓም ጀምሮ በገበያ ላይ እንደሚዉል ደራሲዉ ገልጾአል::

2014 ማርች 11, ማክሰኞ

ግብረ ገብነት ሆይ ማደርያህ ከወዴት ነው? ክፍል ሁለት

ካንገት በላይ ስንስቅበት - የዘመኑ ጥርስ አረጀ፤ ሳቅ ራሱ ጥርስ ናፈቀ - ጥርስም ፈገግታን ጎመጀ፤ ምነው ሰው ሁሉ ሳቅ ራበው! ምነው ሰው ሁሉ ጥርስ አጣ! ቁም ነገር ዳዋ ለበሰ - ህይወት ሆነ የለበጣ! ጥርስ መሳቂያ ጊዜ አጣ - ማኘክ ብቻ ሆነ ስራው! ከልክ በላይ መብላት ለምዶ - ሆዳችን እያስፈራራው! የትውልድ ጥርስ ሻገተ - አጓጉል ስራ በዛበት! ያልሰራንበትን ጎርሰን - የሰው ላብ ስናኝክበት!!! (ግጥም በሞገስ ሀብቱ፤ የጋዜጠኛው ማስታወሻ የተወሰደ) **** ከላይ ያለው ግጥም ግሩም ነው፡፡ ጥርሳችን ፈገግታን ፈልጎ አጣ ይለናል፡፡ ፈገግታም በሙሉ ልቡ የሚስቅበት ጥርስ ፈለገ፡፡ ግን የት ይምጣ፡፡ የሚስቁት ጥርስ የላቸውም፡፡ ጥርስ ያላቸው ደግሞ ማኘክን እንጅ መሳቅ የማይችል /የተሳነው ሆነባቸው፡፡ ከአካላቶቻችን ሁሉ የአዛዥነትን ሚና የሚጫወተው ሆድ ሆነ፡፡ ጥርስም ጌጥነቱን አቆመ፡፡ የሰው ላብ ያለበት የቆሸሸ ነገር ሲያኝክ እንደ በረዶ ጸዓዳ የነበረው ጥርስ ወየበ፡፡ ህሊናም ማሰቡን ትቶ ዙፋኑን ለሆድ ለቀቀ፡፡ ግብረ ገብነትም ከህሊና ጋ አብሮ ጠፋ፡፡ ህሊና ገልብጦ ማንበብ የጀመረለት ግብረ ገብነትም ይገለበጣል፡፡ ባለፈው ሳምንት ካቆምንበት ወሬ አልወጣሁም፡፡ ዛሬም ግብረገብነት ሆይ የት ነህ እያልኩ ነው፡፡ ግብረ ገብነትን በስም ሳይሆን በግብር ፍለጋ እየማሰንሁ ነው፡፡ በቤተሰብም በተቋምም፣ በግልና በቡድን፣ በተማረውና ባልተማረው፣ በሊቁም በደቂቁም፣ በአለቃውም በምንዝሩም፣ በገዢውም በተገዥውም በር ላንኳኳ ነው - ግብረ ገብነት ካለ በማለት፡፡ ድምጼን ከፍ አድረጌ ‹‹ግብረ ገብነት ሆይ ከቶ ከወዴት ነህ!›› እየተጣራሁ ነው፡፡ በየመስሪያ ቤቱ በር ደርዘን ያክል የሥነ ምግባር መርሆዎች ተጽፈው ባየሁበት ቢሮ አቅጣጫ ሁሉ አንኳኳው፡፡ ስማቸው ብቻ እንደ ሙት መታሰቢያ ሀውልት/ ፎቶ ተሰቅሎ አንድም እንኳ ማገኘት ተሳነኝ፡፡ እናም ዛሬ የ12ቱ ስነ ምግባር መርሆዎች አሉበት በተባለው ቦታ ሁሉ ዞሬ ያገኘገሁትን እና የደረስኩበትን የምርመራ ውጤት እንዲህ ሪፖርት ላቀርብ ወደድኩ፡፡ 1. የመንግስት የግዥ ሂደት፡ የግዥ የስራ መደብ ላይ ለመቀጠርና ለመስራት በጣም እድለኛ መሆንን ይጠይቃል፡፡ አሁን በቃ ግልጽ ነው፡፡ ግዥ የስራ መደብን በሀላፊነት ሳይሆን ባበለሙያነት መቀጠር ሎተሪ ከማሸነፍ የላቀ ነው፡፡ ግዥ የስራ መደብ ላይ የሚሰራ ሰው ወዳጁ ብዙ ነው፡፡ በዓመቱ እርሱም የመስሪያ ቤቱን ፍላጎት በማየት ራሱ አቅራቢ ድርጅት ይከፍታል - ይሉኝታ ያለበት በዘመዱ አሊያም በቤተሰቡ አይን ያወጣው ደግሞ በራሱ ስም፡፡ እቃ አቅራቢው ድርጅት ጋ መደራደር በጣም የተለመደ ነው፡፡ ግዥው በቀጥታ፣ በውስንና በግልጽ ጨረታ ሊካሄድ ይችላል፡፡ በቀጥታ ከሆነ ከምትፈልገው ባለሀብት ጋ ትሄዳለህ፡፡ ባለሀብችም ይጠይቃሉ - ‹‹ግዥው በመስሪያ ቤት ነው!›› የመስሪያ ቤት ዋጋ ከፍ ይላል፡፡ ትርፉ ከሁለት ይገመሳል፡፡ ‹‹ላምጪው እንዲከፈል ህግ ያስገድዳል›› ይላሉ የኮሚሽን ሲከፍሉ፡፡ ጀማሪ ገዥ ከሆነ በመጀመሪያው የሰጡትን ይቀበላል፡፡ ልምድ ያለው ባለሙያ ከሆነ ደግሞ ይከራከራል፡፡ ‹እንዴ ይኸ ለኔ ያንሳል፤ ወዳጅነታችንን ማሰብ አለብህ!›› ብሎ አቤቱታ ያቀርባል፡፡ ወይም ደግሞ መተሳሰብ ይጀምሩና የሂሳብ ሊቅ ሊቀጥሩም ይችላሉ፡፡ ባለሀብቱም የሚመጣውን ጊዜ በማሰብ ሳያቅማማ ይከፍላል፡፡ በተሻሻለው የመንግስት የግዥ ደንብ መሰረት አንድ መስሪያ ቤት እንደ ደረጃው ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ግዥ በአንድ አመት በቀጥታ ግዥ ሊፈጽም ይችላል፡፡ በአንድ ጊዜ ደግሞ እስከ 50 ሺህ ብር ድረስ በአማካይ መግዛት እንደሚቻል መመሪያው ያዛል፡፡ በፕሮፎርማ ተሰብስቦ የሚገዛ ከሆነ ድግሞ አንዱን የምትግባባውን ባለሀብት ትመርጣለህ፡፡ ሶስት የዋጋ መሰብሰቢያ ቅጾችን ትሰጠውና ዋጋውን ሞልቶ በተለያየ ማህተም እና ንግድ ፈቃድ በፖስታ አሽጎ ይመልሳል - በለሀብቱ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ዋጋውን ራሱ የግዥ ባለሙያው ሞልቶ በፓስታ አሽጎ ማህተም ብቻ ለማስረገጥ ይሰጠዋል፡፡ ባለሀብቱ የተባለውን ያደርጋል - ግዢው በዚህ መልኩ ይፈጸማል፡፡ በግልጽ ጨረታ የሚካሄዱ ግዢዎች ትንሽ ወሰብሰብ ይላሉ፡፡ እርግጥ ነው ጠቀም ያለ ጉርሻ ያለውም ከዚሁ ግዥ ላይ ነው፡፡ አንዳንዴ ብዙ ሰዎችን ያነካካል፡፡ አሁን አሁን ተጫራቾችም አስቀድመው አለውህ ያላቸው ሰው ከሌለ በስተቀር የጨረታ ሰነድ አይገዙም፡፡ ቢገዙም ሰው ከሌላቸው እንደማያሸንፉ ያውቃሉ፡፡ ጨረታው የተከፈተ እለት የዋጋው ዝርዝር ታይቶ አሸናፊው በሌላ ቀን የሚነገርበት ጊዜ አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ድግሞ ጨረታው ሳይወጣ እንደወጣ ሆኖ አሸናፊው የሚነገርበትም ጊዜ አለ፡፡ እቃው ሳየይገዛ እንደተገዛ የሚሆንበት ጊዜም አለ፡፡ አላስፈላጊ ግዢዎችም ተገዝተው አገልግሎት ሳይሰጡ እቃዎቹ የሚበላሹበት ጊዜም አለ፡፡ በመስሪያ ቤቱ ሀላፊ ስምም የሚገዙበት አጋጣሚም አለ፡፡ እንዲያውም አንድ የክልል ባለስልጣን የነበረ በሀላፊነት ሲመራው በነበረው መስሪያ ቤት ውስጥ አንድ ቡልዶዘር በስሙ በእርዳታ ይሁን በግዥ በስሙ ገቢ ይሆናል፡፡ እናም ይህን ግለሰብ የክልል ቢሮ ሀላፊ መሆኑ አልበቃውም በማለት የሀይለ ማርያም መንግስት የሚኒስተርነት ማዕረግ እድገት ሰጠው ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ የአግልግሎት ዘመናቸው ያለፈባቸው እቃዎችም የሚገዙበት ጊዜ አለ፡፡ በተለይ መድሀኒት ከሆነ ደግሞ አደጋው የከፋ መሆኑ እየታወቀ የሚገዛው ሰው ምን አይነት አዕምሮ ቢኖረው ነው ያስብላል፡፡ በቃ ለሰው ልጅ ገንዘብ ብቻ ዘመዱ የሆነ ይመስላል፡፡ ለማንኛውም ከዚህ ቤት ግብረ ገብነትን አጣሁት፡፡ ግብረ ገብነት ሆይ የት ነህ! ሌላ 12 የስነ ምግባር መርህ የተጻፈበትን ታፔላ አየሁ፡፡ ከዚህ ቤትም ገባሁ፡፡ እንዲህም አገኘውት፡፡ 2. የህንጻ ጨረታዎችን በተመለከተ ብዙ ጊዜ ግንባታዎችን የሚያካሂዱ መስሪያ ቤቶች ገማች መሀንዲስ አካተው ኮሚቴ ያቋቁማሉ፡፡ ተቋራጩ ከመሀንዲሱ ግምት በአስር በመቶ ከፍ እና ዝቅ ብሎ ዋጋ በማቅረብ ሊያሸንፍ ይችላል፡፡ በጣም ዝቅ ካለ አቅም የለውም፤ በጣም ከፍ ካለ ደግሞ የተጋነነ በሚሉ ምክንያቶች ውድቅ ይሆናል፡፡ ገማች መሀንዲሱ የግንባታውን ዋጋ ለመገመት በመጀመሪያ ከሚፈልጋቸው ተጫራቾች ጋር ውሳኔ ያሳልፋል፡፡ በህንጻ ጨረታ ማፈን የምትባል ነገር አለች፡፡ የመሀንዲሱን ግምት ተቋራጩ አስቀድሞ እንዳወቀ ሁለት ወይንም ሶስት ጨረታዎች በተለያዩ ፈቃዶች በስም በታሸገ ኢንቬሎፕ ይቀርባል፡፡ አንደኛው የመሀንዲሱን ግምት የመጨረሻ ዋጋ የያዘ፣ ሁለተኛው ደግሞ የመሀንዲሱን ግምት ከፍተኛ ዋጋ የያዘ ሌላኛው ደግሞ መካከለኛ ይሆናል፡፡ ስለሆነም በመካከል ሌላ ተቋራጭ አለመግባቱ ከታወቀ ሁለቱ አሊያም አንዱ በፈቃዱ ከጨረታ ውጭ ይሆናል፡፡ በሲፒኦ ያሳዙት ገንዘብ ከሚገኘው ትርፍ ጋር ሲነጻጸር አናሳ ስለሚሆን ገንዘቡ ገቢ ይሆንና ጨረታው በከፍተኛው ዋጋ ይሆናል፡፡ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ የህንጻው ጥራት እንዲሁ ይሆናል፡፡ ከልዩ ልዩ ነገሮች ላይ ማጭበርበር ይፈጠራል፡፡ የሲሚንቶውና የጠጠሩ ውህደት መጠን፣ የብረቱ ጥንካሬና ውፍረት፣ መስታዎቶቹ፣ ጅፕሰሙ፣ ቀለሙ… ሁሉም በተገኘው ክፍተት ሁሉ እንደነገሩ ይሆናሉ፡፡ በጣም ቀላል ወጭ የሚያስወጣውን ውሃ እንኳን በደንብ ማጠጣት አይታሰብም፡፡ ህንጻውም አንድ አመት ሳይቆይ አገልግሎት መስጠት ሊያቆም ይችላል፡፡ መንገድም ከሆነ አንድ አመት ሳያገለግል ይፈራርሳል፡፡ በቅርቡ እንኳ በአዲስ አበባ በአንደኛው ሆስፒታል ብዙ ሚሊዮን ብር ተከፍሎት የታደሰው ሆስፒታል አንድ ክረምት እንኳ ሳያገለግል መበላሸቱን በኢቲቪ አይናችን ፕግራም ስንመለከት የዚህን ቤት ግብረ ገብነት አሳሳቢ ያደረገዋል፡፡ አንድ እየተደጋገመ የሚወራ ነገር አለ፡፡ ነገሩ ቀልድ ቢመስልም እውነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ችግሩ የተፈጠረው ገነት ዘውዴ የትምህርት ሚኒስተርነቷን ልትለቅ አካባቢ ነው፡፡ በዪንቨርሲቲዎች የህንጻ ማስፈፊያ ጊዜ አንድ ክፍለ ሀገር ያለ ዩንቨርሲቲ ስድስት ህንጻዎችን አስገነባው ብሎ ሪፖርት ያቀርባል፡፡ በስራ ላይ ጉብኝት ጊዜ አንደኛው ጠፋ ተባለ፡፡ የዩንቨርሲቲው ባለስልጣናትም እንደማያውቁ አብረው ከእንግዶች ጋር ፍለጋ ያዙ፡፡ በመጨረሻ ቦሌ አካባቢ ቆሞ ተገኘ የሚል ቀልድ ይሁን እውነት ሰምቻለው፡፡ እንደ እውነታው ብዙ ባለሀብቶች ተቋራጭነትን የሚመርጡት የምህንድስና ባለሙያ ስለሆኑም፣ ትርፉም ጠቀም ያለ ስለሆነ ብቻ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቹ ተቋራጮች መሀንዲስ አይደሉም፡፡ ይልቁንም ከዚህ ቤት ብዙ ማጭበርበር ስለሚቻል እንጅ፡፡ በአጼው ዘመን የተሰሩ ህንጻዎች ለታሪክ ማህደርነት ወደፊትም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አሁን አሁን ግን የሚሰሩ ህንጻዎች የገንዘብ ፍቅርና አለመታመን ተጨማምረውበት ሁለት አስርት አመታትንም መድፈን አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ በተለይ በመንግስት የሚገነቡ ተቋማት ጉዳይ አሳሳቢ ነው፡፡ ጤና ጣቢያዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ዩንቨርሲቲዎች፣ ቢሮዎች፣ አውራ መንገዶች … እነዚህ ሁሉ የጥራት ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ በዚህ ሰፈር ከአስራ ሁለት ምግባር አንድም ጠፋ፡፡ ታማኝነት፣ ቅንነት፣ የህዝብ አገልጋይነት…፡፡ አይገርምም!! ግብረ ገብነት ሆይ የት ነህ!! አሁንም ሌላ ‹‹ደንበኛ ንጉስ ነው›› የሚል ጽሁፍ የተሰቀለበት ቢሮ እያዘገምኩ ነው፡፡ በር አካባቢ ‹ግብርን በመክፈል የህዳሴ ጉዟችንን እናፋጥን› የሚል ባነር በር አካባቢ ያየሁበት ቤት ነው - ገቢዎችና ጉምሩክ፡፡ 3. ገቢ ግብር መጽሀፍ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሄርን ለእግዚአብሄር ይላል፡፡ በዚህም የሰራ ሁሉ እንደገቢው ግብር ይጣልበታል፡፡ መንግስት ሰራተኛው ከደመወዙ ላይ ይወሰዳል፡፡ ችግሩ ያለው ከነጋዴው ነው፡፡ ነጋዴ ልዩ ግብር ይጣልበታል - በመንግስት፡፡ በስራውም በሚያስወጣቸውና በሚያስገባቸው ሸቀጦችም እንዲሁ፡፡ አንደ ሰው ገቢዎችና ጉምሩክ ስራ ከገባ ‹የእንኳን ደስ አለህ› መልዕክት የሚመጣው ከብዙ አጃቢዎቹ ዘንድ ነው፡፡ በተለይ በሚገቡና በሚወጡ እቃዎች ላይ ያለው ማጭበርበር ቀላል እንዳልሆነ በአይንም የምናየው በሀሜትም የምንሰማው ነው፡፡ ከፍተኛ ባለስልጣኖቻችንም በዚህ ዓመት ቃሊቲ የወረዱት በዚሁ አይደል!! ገቢዎችና ጉምሩክ የሚሰሩ የነበሩ አሁን የናጠጡ ባለሀብች ሆነዋል፡፡ በክልል ገቢዎች የሚሰበሰቡ የስራ ግብር በቁርጥና በስሌት ለመጣል ሲታሰብ አሁንም ከላይ ካየናቸው የተለየ አይደለም፡፡ የግብር ግምት እና ክትትል ባለሙያዎቹ፣ የስራ ሂደት መሪው፣ ኦዲተሩ ሁሉም እነርሱ እንዳደረጉት ይሆናል፡፡ ባለሀብቱ ከባለስልጣኑ ጋር ከተስማማ በሚሊዮን የሚከፍለው ወደ ሽዎች ዝቅ ይደረግለታል፡፡ ባለሙያው በጎን በኩል የባለ ሀብቱ የግል ሂሳብ ሰራተኛ ይሆንና ከታክስ እንዴት ማምለጥ እንደሚችል ይሰራለታል፡፡ ይህን ያደረገው ባለሙያም ለስራው ይሸለማል፡፡ በቃ ሂዎት እንዲህ ነች፡፡ የገቢ ክትትል ባለሙያው የተሳሳቱ መረጃዎችን ለግብር ገማቹ ባለሙያ ያቀብላል፡፡ የግብር ገማቹ ባለሙያ ደግሞ ከገቢ ክትትል ባለሙያው የሚመጡትን መረጃዎች ያድበሰብሳቸዋል፡፡ ኦዲተሩ ከሁሉም የተዘለሉትን እርሱም ይዘላቸዋል፡፡ የስራ ሂደት በለሙያውና የቢሮው ሀላፊ ደግሞ ከፍተኛ ግብር ከፋዮችን ይከታተልና እንደሚሆን ያደርጋል፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና በችርቻሮ የሚተዳደሩ ሰዎች የንግድ ድርጅት በጥቃቅን ስህተት ሊታሸግ ሲችል ከፍተኛ ገቢና ትልቅ ድርጅት ያላቸውን ሰዎች ግን ከጥቃቅን ባለሀብቶች ላይ እንደፈለገ የማድግ ስልጣን የነበረው ባለሙያው የመናገር ስልጣን የለውም፡፡ ገንዘብ አሊያም ባለስልጣን ዘመድ ያለው በለሀብት የፈለገውን ያደርጋል፡፡ ቫት ሊያጭበረብር፣ ገቢው ሊደብቅ ይችላል፡፡ ፍርድ ቤት ሌባ እስካላለህ ድረስ በየትም የተገኘ ገንዘብ ይሁን ሀብትህ ነው፡፡ ባለሀብቱም፣ ባለሙያም፣ ባለስልጣኑም ተባብረው ለመንግስት ገቢ የሚሆነው ገንዘብ ይወስዱታል፡፡ መንግሰት መንግስትን ይሰርቃል፤ ህዝብ ህዝብን ይሸውዳል፡፡ የዚህ ቤት ገብረ ገብነት ይህ ነው፡፡ የተባለውን ላለመክፈል ያቅማማ ባለሀብት አገር ካልቀየረ በስተቀር መስራት አይችልም፡፡ ውሃ በቀጠነ ማስፈራሪያ ይደርሰዋል፡፡ እርግጥ ነው የተሰበሰበውም ገንዘብ አግባብ ላይ ይውላል ማለት አይቻልም፡፡ ግን በየቦታው ይመዘበራል፡፡ ታዋቂው የስነ ጽሁፍ ሰው ሸክስፒር እንዲህ አለ፡ ምናልባት ገንዘብ እድሜን አያራዝም ይሆናል፣ አሊያም እርሱ ያልደረሰበት ፍልስፍና ነው፡፡ ሸክስፒርም ይቀጥል፡ Life is cycle which turns on the wheel Starts on the womb ends on the tomb If life is a thing which money would buy The rich will live and the poor will die But nature in its wisdom made it too The rich and the poor together must go!! አይ እግዚአብሄር ደጉ ሀብታምንም ደሀንም አንድ ማድረጉ በጀን፡፡ እንጅማ!! ሰው የገንዘብ ባሪያ ሆነ ማለት ይህ ነው፡፡ በየትኛውም በኩል ይምጣ ብቻ ገንዘብ ይሁን፡፡ የሰው ህይወትም ለውጥ ይሁን፡፡ አዎ ገንዘብ ገንዘብ ገንዘብ፡፡ የዚህ ትውልድ አደገኛ አካሄድ ፍቅረ ንዋይ ነው፡፡ ግብረ ገብነት ከዚህ ቤት አጣሁት አሁን ፍለጋውን እቀጥላለሁ፡፡ አንድ ቀን አንድ ቦታ ላገኘው እችላለሁ ብየ ተስፋ በማድረግ፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት ሌላ ቤት አንኳኳለው፡፡ እስከዚያው መልካም ሳምንት!! ይቀጥላል!! ሰላም

2014 ማርች 10, ሰኞ

ጉድ በል ጎንደር- ‹የመለስ ካምፓስ› በጎንደር ዩንቨርሲቲ!!

አስታውሳለሁ በ1999 ዓ.ም. የጎንደር ዩንቨርሲቲ አንደኛው ካምፓስ ስም ይሰጠው ተባለ እና ተማሪው ሁሉ ተወራከበ፡፡ ከማራኪ ካምፓስ በታች በኩል ያለው ካምፓስ ስያሜ ብዙ አጨቃጨቀ፡፡ ከዚያም ተማሪዎች ፊርማ አሰባሰቡ- አጤ ቴዎድሮስ ካምፓስ ይባል ተባለ፡፡ ከዩንቨርሲቲው አመራሮቸች ጋ ‹‹የነፍጠኛ ስም›› ነው የሚል ቅራኔ ቢኖርም በጊዜው ከነበረው የፖለቲካ ትኩሳት አንጻር ያን ስያሜ መቃወም ማለት አላስፈላጊ ብጥብጥ መፍጠር ነበር - እናም ስያሜው ጸደቀ፡፡ የከተማ ታክሲዎች አንዳች አገራዊ ፋይዳ ያለው አዋጅ እንደታወጀ በመቁጥር ‹‹አጼ ቴዎድሮስ ካምፓስ›› የሚል ወረቀት ጽፈው በጣም አስተዋወቁት፡፡ ከዚያ በኋላ ጎንደር ተረት የሆኑ ነገስታቶቿን ለማስታዎስ ይመስላል አሁንም ሌላኛውን ካምፓስ ‹‹ፋሲል›› ካምፓስ ተባለ፡፡ ከአመታት በኋላ ደግሞ ከከተማው ወጣ ብሎ ሌላ ካምፓስ ተገነባ፡፡ ይህ ካምፓስ ከከተማው ትንሽ ወጣ ያለ በመሆኑ ከተማሪ ትክተት ውጭ ነው፡፡ የዚህን ካምፓስ ስያሜ ለማውጣት ግን ተሜን ማማከር እንደቀድሞ አስፈላጊ አልነበረም፡፡ ከዩንቨርሲቲው ሴኔት ይሁን ከፌደሬሽን ምክር ቤት በተላለፈ ውሳኔ ‹‹መለስ ካምፓስ›› ተባለና በቅርቡ ተመረቀ፡፡ ግልጽ መሆን የነበረበት ለምን መለስ መባል እንዳስፈለገው ነው፡፡ መለስ በየሀገሩ ሁሉ ብዙ ቦታ ተሰይሞለታል፡፡ ‹መለስ ፓርክ፣ መለስ ሆስፒታል፣ መለስ ትምህርት ቤት፣ መለስ ጤና ጣቢያ፣ መለስ....› ብዙ መለስ የሚባሉ ቦታዎች ከከጋምቤላ እስከ ቶጎጫሌ፣ ከዛላንበሳ እስከ ሞያሌ ድረስ አሉ፡፡ በሁሉም አቅጣጫ ቢያንስ በአማካይ 10-20 ኪሌ ሜትር ርቀት ያለማጋነን በመለስ ስም የተሰየመ ነገር አይታጣም፡፡ በአማካይ 10-20 ጫማ ርቀት ደግሞ ስለ መለስ ራዕይ የሚሰብክ ሰው አይታጣም፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ ስለምን ዩንቨርሲቲውን መለስ አሉት ቢባል መለሱ ግራ ያጋባል፡፡ ምናልባትም ‹መለስ የተማረ ሰው ስለሚወዱ› የሚል ካለ ተሳስቷል፡፡ ምክንያቱም በመጀመሪያ ከደደቢት በረሃ አራት ኪሎ ሲደርሱ አቶ መለስ ያደረጉት ነገር ቢኖር 44 በላይ ‹‹አሉ የተባሉትን›› የሀገሪቱን ምሁራንና ተመራማሪዎች ነው ድራሽ ያጠፋቸው፡፡ (በዚህ ሰዓት ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የተባረሩ ሰዎችን ዝርዝር እያየሁ ነው ያሰብኩት፡፡) ተያይዞም የጎንደር ዩንቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት መለስ ከሞቱ ቀደም ብሎ በመኪና አደጋ ህይወቱ ሲያልፍ ሌላው ለጎንደር ህዝብ አጠያያቂ አሟሟት ነበር፡፡ ምናልባትም አሁን በጎንደር አንድ ካምፓስ የተጀመረው ስያሜ አዲስ አበባ ባሉት ሁለት ዩንቨርሲቲዎችም አንደኛውን ሙሉ በሙሉ ዩንቨርሲቲው ‹‹መለስ ዩንቨርሲቲ›› ሊባል እንደሚችል ከወዲሁ መገመት አያዳግትም፡፡

2014 ማርች 7, ዓርብ

ሰበር ዜና- በሰሜን ጎንደር ከ50 በላይ ሰዎች ታሰሩ፡፡



በሰሜን ጎንደር ዞን በጭልጋ፣ በአርማጭሆና በመተማ ወረዳዎች እና በአካባቢው ያሉ ከ50 በላይ ሰዎች ትናንት ማምሻውን በታጣቂ ሀይሎች ታፍነው መወሰዳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የተያዙት ግለሰቦች ከአካባቢው ራቅ ወደለ ቦታ መወሰዳቸውን የታሳሪ ቤተሰቦችና ወዳጆች  ይናራሉ፡፡ ለምን እንደታሰሩ ለማጣራት የተደረገው ሙከራ እስካሁን አልተሳካም፡፡

2014 ማርች 6, ሐሙስ

የጎንደር ትኩሳቶች- የቅማንት የማንነት ጥያቄና የድንበር ውዝግብ


 
በከተማው መንፈሴን የሚይዝ ቦታ ፈለግኩ፡፡ ቋራ ሆቴል በረንዳ ላይ ተቀምጬ መጻፊያ ወረቀት ከፖርሳዬ አውጥቼ ቀና ስል ከኔ በላይ የሆኑ ቦታዎችን ተመለከትኩ፡፡ ስለሆነም ወደ ሰማዬ ሰማያት ትንሽ ጫማም ቢሆን ከፍ ማለት ሻትኩ፡፡ ባጃጅ ተኮናተርኩና ወደ ጎሃ ሆቴል በሶስት እግር ሮጥኩ፡፡ ጊዜው ከተሲያት ነው፡፡ ጎሃ ተራራ ላይ ተቀምጬ በሁሉም አቅጣጫ አማተርኩ፡፡ ከእኔ በታች አንዲት አሮጌ ከተማ አለች፡፡ በጣም ያረጀች፡፡ ስሟም ጎንደር የአጼ ፋሲለደስ መዲና፡፡
ከጎንድር ከተማ አናት ላይ ሆኜ ስለ ጎንደር መፍትሄ ስራይ ያልተገኘላቸው ትኩሳቶች እንዲህ እየጻፍኩ ነው፡፡ ጎንደር ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ለዬት ያሉ ሁለት አንገብጋቢ ትኩሳቶች ከፊቷ ተጋርጠውባታል፡፡ የቅማንት ብሄረሰብ የማንነትና ራስ አስተዳደር እንዲሁም የድምበር አከላል ጉዳይ፡፡ ሁለቱም እስካሁን መፍትሄ አልተሰጣቸውም፣ ሁለቱም ፍጹም ጡዘት ላይ ደረስዋል፡፡ ሁለቱም ታላቅ አገራዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡
የድንበር አከላሉ ሁለት መልክ አለው፡፡ አንደኛው ከትግራይ ክልል ጋር አጎራባች በሆኑ በአብርሃ ጅራ፣ አብደራፊና በአካባቢው ያለው ሲሆን በዚህ አካባቢ ያሉ ቀበሌዎችን ወደ ትግራይ ክልል ለመደባለቅ በሚደረገው እንቅስቃሴ ተፈናቀልን ያሉ የሰሊጥ አምራች ገበሬዎች እና ኢንቨሰተሮች ችግር አለ፡፡ ይህ ችግር አይደለም ባይባልም አገር እስካለች ድረስ ከሁለተኛው የድንበር ችግር አንጻር አንገብጋቢ ላይሆን ይችላል፡፡
ከባዱ የኢትዮ ሱዳን የድንበር ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ብዙ ፓለቲከኞችና ጸሀፍት ኢህአዴግ ‹አያደርገውም› ‹ያደርገዋል› እያሉ ሁለት የተለያዩ መላ ምቶችን ሲያስቀምጡ ሰነባብተዋል፡፡ ምንም እንኳ ጉዳዩን ኢህአዴግ እና ጊዜ የሚፈቱት ቢሆንም ኢህአዴግ ድምበሩን አሳልፎ ለሱዳን አይሰጥም የሚል ግምት የለኝም፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ በ1969 አካባቢ የዚያድ ባሬ መንግስት የምስራቅ ኢትዮጵያን እስከ ድሬ ደዋ ድረስ በእብሪት ሲወር የሶማሊያን አቋም በመደገፍ የኢትዮጵያ መሬት ስላልሆነ ወረራው አግባብነት አለው በማለት ከባዕድ መንግስት ጎን መቆሙን የፖለቲካው እስረኛ አንዷለም አራጌ ‹ያልተኬደበት መንገድ› በሚለው መጽሀፉ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በዚህ እሳቤ የአሁኑ መሬትም በሰሜን ምዕራብ መገኘቱ ካልሆነ በስተቀር ምንም ልዩነት ስለሌለው ‹መሬቱ የሱዳን መንግስትና ህዝብ ነው› ብሎ ሊያስረክብ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ምናልባት የሚረከብበት ጊዜና የሚረከበው መሬት ነው በውል ያልታወቀው፡፡ (የሚወራውን ያክል መሬት ለባዕድ ተላልፎ ከተሰጠ ግን የሚያሳዝነው እነ አጼ ቴዎድሮስ የተወለዱበትን እና የሸፈቱበትን ቦታ እንዲሁም አጼ ዮሀንስ በመሀዲሰት ጦር አንገታቸውን የተቆረጠበትን ቦታ ለመጎብኘት የሱዳን ፓስፖርት ማገኘት ግድ የሚለን ጊዜ ሲመጣ ማዬት ነው፡፡ መሀዲስቶችም ጎንደርን ካቃጠሉ ከ120 ዓመት በኋላ መልሰው ጎንደር ወሰዱ ማለት ነው፡፡ ጣሊያን ከ40 ዓመት በኋላ መጥቶ እንደተሳካለት ሁሉ!!)
የድንበሩን ጉዳይ ገታ እናድርግና ወደ ሌላኛው የጎንደር ትኩሳት እንለፍ፡፡ የቅማንት ብሄረሰብ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ሌላው አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ አገኝቸዋለሁ፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት አባ ወንበሩ መርሻን ጭልጋ ወረዳ ገጠር ድረስ ሂጄ አነጋግሬያቸዋለሁ፡፡
የቅማንት ህዝብ ከአገው ህዝቦች እንዳንዱ የሚቆጥሩት አሉ፡፡ አገዎች በኤርትሪያ (ብሌን)፣ በወሎ (ዋግኸምራ)፣ በጎንደር (ቅማንት) እንዲሁም በጎጃም (አዊ) ይኖራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ያሉት አገዎች ከቅማንት ውጭ ሁሉም ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድራሉ፡፡
የቅማንት ህዝብ በብዛትና አልፎ አልፎም ቢሆን በጭልጋ፣ በጎንደር ዙሪያ፣ በደንቢያ፣ በደጋው ቋራ፣ በላይ አርማጭሆና በመተማ ይኖራል፡፡ ቋንቋው በመጥፋት ላይ ቢሆንም የሚናገሩ በእድሜ ገፋ ያሉ ሰዎችን አግኝቻለሁ፡፡ አብዛኛው (ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል) ህዝብ የኦርቶዶክስ ክርስትና አማኝ ነው፡፡ ክርስትናቸው የቅርብ ጊዜ መሆኑንና ቀደም ሲል ወደ ኦሪት እምነት የቀረበ እንደነበር አባወንበሩ ይናገራሉ፡፡ ‹ወንበር› በቅማንት እምነት የመጨረሻው የተከበረ ሰው ማዕረግ ነው፡፡ ስለሆነም ‹ቅማንት› የሚለው የሀይማኖትም፣ የቋንቋም፣ የባህልም መገለጫ ነበር፡፡ አሁን አሁን ቅማንት የማንነትና የቋንቋ መገለጫ ይሆን እንደሆን እንጅ የሐይማኖት ሊሆን የሚችል አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ነበሩን እምነት የሚከተሉ ሰዎች በቁጥር እጅግ በጣም አናሳ ናቸው፡፡ የአባ ወንበሩም ልጆች ሳይቀር ክርስትያን መሆናቸውን ነገረውኛል፡፡
በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 39/5 ላይ አንድ ህዝብ በተያያዘ መልክዓ ምድር ሆኖ አንድ አይነት ታሪካዊ አመጣጥ ካለው፣ የስነ ልቦናና የራሱ የሆነ መገለጫ ካለው ራሱን በራሱ ሊያስተዳድር እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ በዚህ እሳቤ እንደኔ እምነት የቅማንት ህዝብ ማንነቱ እንዳይታወቅ የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ የህዝቡን ቋንቋና ባህል መጠበቅ ሀገራዊ ሀብት ይመስለኛል፡፡
ሆኖም ግን እስካሁን መፍትሄ ሳይሰጠው መቆዬቱ የተወሳሰቡ ችግሮችን እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ችግሩን ያወሳሰበው ደግሞ የህወሓት/ኢህአዴግ ሁለት መልክነት ይመስላል፡፡ ኢህአዴግ እንደ ‹አማራ› እና ‹እንደ ህወሓት› ዓይነት ሁለት መልኮችን ለብሶ የቅማንትን ህዝብ ችግር በጣም አወሳስቦታል፡፡ ይህም ሌላው ‹ለአማራ ህዝብ የተቀበረ ፈንጅ› አድርጎታል፡፡ ይህን በተጨባጭ አመክንዮ እንመልከት፡፡
በሁለተኛው የህዝብ ቆጠራ በ1984 ዓ.ም. በተገረገው የቅማንት ህዝብ ወደ 172000 አካባቢ የነበረ ሲሆን በ1999 ዓ.ም. ደግሞ ቅማንት የሚለውን ማንነት ሰርዞ ‹አማራ› በሚል ሰር እንዲቆጠሩ አደረገ፡፡ ይህ የመጀመሪያው ሴራ ነው፡፡ ከዚያም ይህን የኢህአዴግ ሳይሆን ‹የትህምከተኛ› አማሮች ሀሳብ መሆኑን እራሱ ህወሓት በሚያንቀሳቅሳቸው ደረ ገጾች እንዲቀጣጠል አደረገ፡፡ በፈረንጆች አቀጣጠር በጁላይ 12 ቀን 2013 አንድ በብዕር ስሙ ምዝገና አደራ የተባለ ሰው “Unfinished Amharization Process in Ethiopia and Qimants Quest for Dignity and Self Rule” በሚል ርዕስ በtigraionline.com ባስነበበው ጽሁፍ የአማራን ህዝብ ሲከስ ‹‹በሚኒሊክ የተጀመረው ህዝብን በግዳጅ አማራ የማድረግ ሂደት እስካሁን አልተቋጨም፡፡ አሁንም በግዳጅ ሰዎችን የአማራ ህዝብን ቋንቋና ባህል እንዲቀበሉ በማስገደድ በአማራ መንግስት እንዲተዳደሩ ማድረጉ እንደቀጠለ ነው፡፡ ... የአማራ ፈላጭ ቆራጮች አሮጋንት አማራዎችን በያዘው በካንጋሮ ፓርላማቸው እያስቀጠሉት ነው፡፡ ሆኖም ግን የማንነታችን ጥያቄ መልስ እስከሚያገኝ እንዲሁም ከአማራ ቅኝ ግዛት እስክንወጣ ማንኛውንም አይነት የትግል ስልት እንጠቀማለን፡፡›› (የተሰመረበት ከራሴ)
ምናልባትም ይህን የጻፈው አንድ የህወሓት ጀሌ ሊሆን ይችላል ብዬ አስቤ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም አንድ ባለ 100 ገጽ ‹የቅማንት ህዝብ የማንነት ጥያቄ እና የኢፈድሪ ህገመንግስት› የሚል አሁንም በብዕር ስሙ ትንቢቱ ደረሰ የሚባል ሰው የጻፈውን መጽሀፍ ሳነብ ተመሳሳይ መልዕክት ያለውና በተለይ ‹አማራውን› ሙልጭ አድርጎ እንደ ሰሞኑ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ተብዬ የሚሰድብ ሆኖ አገኝቸዋለሁ፡፡
ሌላው የቅማንት ብሄረሰብ የማንነት እና የራስ አስተዳደር ይፈቀድልኝ አስተባበሪ ኮሚቴ በ1999 ዓ.ም. ከተቋቋመ በኋላ በተከታታይ ለክልሉ መንግስት እንዲቀርብ ተደረገ፡፡ በ2003 ዓ.ም. በክልሉ መንግስት ጥናት ተደርጎ ከ6645 በላይ ቋንቋውን ተናጋሪ ሰዎች ቢገኙም ቋንቋው እንደሞተ በመቁጠር ሰላማዊ ሰልፍ እንኳ እንዳይወጡ እስከዚህ ዓመት ድረስ እንዲቆዩ ሆነ፡፡

ስለ ብሄረሰቡ መኖር በርከት ያሉ ሰዎች ጥናትና ምርምር አድረገዋል፡፡ በጎንደር ዩንቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፐሮፌሰር ይግዛው ከበደም ተመሳሳይ ጥናት አቅርበዋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም የብሄረሰቡን መኖር የሚያረጋግጡ ጥናቶች ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ተደርጓል፡፡ ይህም አስተባባሪ ከሚቴዎችንና አንዳንድ የህብረተሰቡን ህልውና መኖር የሚፈልጉ ወገኖችን በእጅጉ አስቆጥቶ በአማራ ህዝብ ላይ በጥላቻ እንዲነሱ አደረገ፡፡
በሳለፍነው ሳምንት እሁድ የካቲት 2006 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ በተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ ሁለት ተቃራኒ ሀሳቦች ተንጸባርቀዋል፡፡ አንደኛው ህወሓት/ኢህአዴግን መደገፍ ሲሆን ‹አማራ ኢህአዴግን› ደግሞ መቃወም ነው፡፡ የክልሉን መንግስትና ህዝብ እንቃወማለን የሚሉ ወገኖች በሌላ በኩል የመለስን ፎቶ ግራፍ በመያዝ ‹‹የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ራዕይ እናስፈጽማለን›› የሚለ መፈክሮች ይሰሙ ነበር፡፡ (በጊዜው በጎንደር አቢዮት አደባባይ ከ20-30 ሺህ የሚገመት ሰው ለሰልፉ ከተለያዩ ወረዳዎች ወጥቶ ነበር፡፡)
አሁን የኢህአዴግ ሁለት ገጽታነት በጉልህ የታዬ ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ ‹በአማራነቱ› ቅማንትን ማጥፋትና አስገድዶ አማራ ማድረግ፣ ሰላማዊ ሰለፍ መከልከል ሲሆን በ‹ህወሓትነቱ› ደግሞ የተከለከሉበትን ምክንያት ከአማራው ህዝብ አሮጋንትነት ምክንያት ነው በማለት ድረ ገጾችን በማመቻችት የጥላቻ መርዝ መዝራት ነው፡፡
የቅማንት ብሄረሰብ የማንነት ጥያቄ የመጨረሻ ጡዘት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አሁን ህወሓት/ኢህአዴግ የሚፈልገውን ራዕይ ለማሳካት የበቀሉ ፍሬ ሲያፈራ ማዬት ብቻ ይሆናል፡፡
ጥያቄ አቅራቢዎቹ በሰሜን ጎንደር ባሉ ስምንት ወረዳዎች (ጎንደር ከተማን ጨምሮ ወገራን፣ ላይ አርማጭሆን፣ ጎንደር ዙሪያን፣ደንቢያን፣ ጭልጋን፣ ቋራንና መተማን) 126 ቀበሌዎችን በልዩ ዞኑ እንዲካተቱ እና ጎንደር ከተማ አዲስ የሚመሰረተው የቅማንት ልዩ ዞን ከተማ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ ምንም እንኳ ማረጋገጥ ባልችልም ጎንደር ከተማ ሁለት ከተማ አስተዳደር እንዲሆን ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ አዘዞ ከተማ አስተዳደርና ጎንደር በሚሉ፡፡ እንደሚባለው ከሆነ አንደኛው ከተማ ለልዩ ዞኑ ከተማነት ያገለግላል፡፡
እንደ መውጫ
የቅማንት ብሄረሰብ የማንነት ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ነገር ግን የሁሉንም ህዝብ ፍላጎት ያገናዘበ መሆን ይኖርበታል፡፡ ተወደደም ተጠላም አንዳንድ ጉዳዩን የያዙ ሰዎች ሕወሓቶችን የሙጥኝ ቢሉም ቅሉ ለቅማንት ህዝብ በአካባቢው ያለው የተዋለደውና የተዛመደው ጎንደሬ እንጅ ሌላው የሚቀርበው አይመስለኝም፡፡  
ሌላው የብሄረሰቡ ልዩ ዞን በሚካለልበት ጊዜ የአብዛኛውንም ህዝብ መብት በሚረግጥ መልኩ መሆን እንደሌለበት መንግስት ሊያስብበት ይገባል፡፡ ጭልጋ ወረዳ ላይ አብዛኛው ቅማንት ቢሆን ወገራ ላይ አሊያም ደንቢያ ላይ ትንሽ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም የብዙሀኑን ጥያቄም ግንዛቤ ያስገባ መሆን አለበት፡፡ የጎንደር ከተማ እጣፈንታም አስቸጋሪ ይመስላል፡፡ እንደ ማዕከላዊ እስታስቲክ ከሆነ የጎንደር ከተማ ህዝብ ከ85 ፐርሰት በላይ የአማራ ህዝብ ያለበት ከተማ ነው፡፡ ከ6 ፐርሰንት በላይ የሚሆነው ደግሞ የትግራይ ብሄረሰብ ነዋሪ ነው፡፡ ስለሆነም የ85 ፕረሰንቱን ህዝብ ፍላጎት ጥሶ የሚጸድቅ ከሆነ አስቸጋሪነቱ ብዙ መልክ ይኖረዋል፡፡
ማንነት ክብር ነው፡፡ ማንነትን ለማግኘት ግን የሌላውን ማንነትም መረገጥ አደጋ አለው፡፡
ሰላም፡፡

2014 ማርች 5, ረቡዕ

ግብረ ገብነት ሆይ ማደርያህ ከወዴት ነው!

ክፍል አንድ

እሪ በይ ኢትዮጵያ - ቅል ድንጋይ ሰበረ!
ውሃ ሽቅብ ወጣ - ዘመን ተቀየረ!
ሌባ እየከበረ - ነጋዴው ከሰረ!
ሀገር ፈራረሰች - ድንበር ተደፈረ!
እንደ ቅርጫ ስጋ - እየተመተረ!
ለአርብ ለድርቡሹ - ይታደል ጀመረ!
ጀግና አንገቱን ደፋ - ባንዳ ተወጠረ!!
(ግጥም፡ የማለውቀው ጸሀፊ)
******
ግብረ ገብነት ወይም የስነ ምግባር ትምህርትን ከማንም የበለጠ ከቤተሰቦቻችን እንማራለን፡፡ አንድን ነገር፣ ሀሳብ ወይም ድርጊት በጥሩና በመጥፎ፣ በጽድቅና በሀጢያት፣ በቅድስና እና እርኩሰት፣ … እየከፋፈልን የምናይበት ሂደት ነው- ግብረ ገብነት፡፡ እርግጥ ነው ለአንዱ ጽድቅ የሆነው ለሌላው ሀጢያት፣ ለአንደኛው የመልካም የሆነው ለሌላው መጥፎ አሊያም ደግሞ ለአንዱ ጥሩ ለሌላውም ጥሩ፣ ለአንድም ለሌላውም ጽድቅ ሆኖ የሚቆጠር ነገር ይኖራል፡፡ በነገሮች ላይ ያለን ጽንፍ አመለካከት ከባህል ባህል፣ ከቦታ ቦታ፣ ከሀይማኖት ተቋም ሀይማኖት ተቋም፣ ከቤተሰብም ቤተሰብ ሊለያይ እንደሚችል በዘርፉ በተለይም በስነ ባህል (Folklore) እና በ Cross Cultural Psychologists የተሰሩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
የግብረ ገብነትን ትምህርት በየትኛውም ህብረተሰብ ለማስረጽ የቤተሰብና የሀይማኖት ሚና ወሳኝ ነው፡፡ የሀይማኖት ተቋማት የማናየውን (በእምነት ብቻ የምናየውን) ዓለም ለመውረስ በጽድቅና ኩነኔ፣ በጥሩና መጥፎ፣ መካከል ያለውን ልዩነት ድንበር በማበጀት ለምዕመኖቻቸው አንድም በስብከት አሊያም ቅዱሳን ድርሰቶቻቸው ያስተምራሉ፡፡ እምነትም ያለስራ የተወገዘ መሆኑን አጽንተው ይሰብካሉ፡፡ ሰባኪውም በግብሩ ሞዴል የሆነለታ ጻድቅነት ይሰጠዋል -ወይ በአምላክ አሊያም በሰው፡፡
ይህ የግብረ ገብነት ትምህርት ከልጅነታችን ጀምሮ እየተማርን ስለምንመጣ የስብዕናችን አካል የመሆን እድሉ የሰፋ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ግብረ ገብ ለመሆን የግድ የተጻፈ ህግ ላያስፈልገን ይችላል፡፡ ህሊናችን በራሱ ችሎት መዝኖ ፍርዱን ይሰጠናል፡፡ ‹‹መጥፎ›› ስንሰራ ህሊናችን ሲቀጣን፣ ‹‹ጥሩ›› ስንሰራ ህሊናችን ‹‹ጎሽ›› ሲለን ከምድራዊው ህግ ይልቅ ሰማያዊውን ዓለም ስንናፍቅ፣ ሰማያዊውን አካል ስንፈራ ህይወታችን እንቀጥላለን፡፡ አንዳንዴ ታዲያ ይህችን ‹‹መጥፎ›› የሆነች ነገር ደጋግመን የሰራን እንደሆን ‹‹ሀጢያትነቱን›› እንረሳና እንደ ‹‹ጽድቅ›› በመቁጠር አሁንም እንቀጥላለን - ምንም እንኳ በሌላው ዘንድ ‹‹ህሊና ቢስ›› ብንባልም፡፡
ይህን የህግ ጥሰት የሚሰሩት ደግሞ ስለ ግብረ ገብነት የሚሰብኩና የሚያሰለጥኑ ግለሰቦችና ተቋማት ከሆኑ ‹‹ህሊና ቢስ›› በሚል ብቻ አይታለፉም- በምዕመኑ /ሰልጣኙ ‹‹አጃአይቭ›› ይባላል፡፡ ‹‹እነ እከሌ ያላከበሩትን እንዴት እኛ!›› የሚል ነገር ይነሳል፡፡ ከዚያም ጥሰቱ ይቀጥላል፡፡ በመጨረሻ ወደተቀደሰው ነገር ይቀላቀላል፡፡ ‹‹እርኩሱ›› ‹‹ቅዱስ›› ሆነ ማለት ነው - ‹በለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም› እንዲሉ፡፡ ህግ አውጪው ያልተገበረውን ህግ ፈጻሚው እንዴት ይቻለዋል!! በዚህ መልኩ ብዙ ነገሮች ከጊዜ ጊዜ ይቀያየራሉ፡፡ እነዚህ ለውጦች አንዳንዴ ሲጠቅሙን ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲጎዱን ይኖራሉ፡፡ ጥቅሙ አዲስ አስተሳሰብን በቶሎ እንድንላመድ፣ ያልታሰበን እንድናስብ ያደርገናል፡፡ ‹ንጉስ አይከሰስም ሰማይም አይታረስም› የሚለውን አስተሳሰብ ንጉሱን ለመገልበጥ በተደረገ ሙከራ ህብረተሰቡ ለካ ንጉስም ይቀየራል ወደማለት ይሸጋገርና በህዝብ የተመረጠ መንግስት ለመመስረት እንቅስቃሴ እንደሚጀመረው ሁሉ (ምንም እንኳ እስካሁን እኛ እድለኛ ባንሆንም -ባይሳካልንም)፡፡ ሰማይ አይታረስም የሚለውን አስተሳሰብ በአውሮፕላንና በሮኬት ወደ ህዋ ምጥቀት ህዋን ለማሰስ እንደተቻለው ሁሉ፡፡ ከዘመናት በፊት ‹‹የአስኮላ›› ትምህርት ‹‹የሰይጣን ነው›› የሚባለውን እንደረሳነው ሁሉ፡፡ ብዙ ነገሮች እንደቀየርናቸው ሁሉ፡፡
ብዙ ‹‹መጥፎዎች›› ወደ ‹‹ጥሩነት›› ተቀይረዋል፡፡ እኔን ዛሬ እንደጽፍ ያነሳሳኝ በስህተት ወይም በአለማወቅ ቀድመው ‹በሀጢያት› ተፈርጀው በኋላ ላይ ቦታቸውን ያገኙ እና ጥሩ ለውጥ ያመጡትን አስተሳሰቦችና ድርጊቶች አይደለም፡፡ በዚህ ሰበብ ከምርቱ ጋር የመጣ ገለባ እና ከስንዴው ጋር የተደበላለቀው እንክርዳድ ነው፡፡ እንዚህን ሊለዩ/ ሊያበጥሩ የሚችሉ መንሽና ማንካ ያነሳቸው የሞራል ገበሬዎች በርካታ እየሆኑ መጥተዋል፡፡
አንዳንዴ ስለሞራል ሳስብ እናቴንና አባቴን ሁሉ እስከመውቀስ የደረስኩበት ጊዜ አለ፡፡ አስታውሳለሁ እናቴ ‹‹የሰው ገንዘብ ቤታችንን አይከፍለውም›› የሚለውን ምክር ከሺህ ጊዜ በላይ ነግራኛለች፡፡ ገንዘብ ሳገኝ ለባለቤቱ እንድመለስ አሊያም ባለቤቱ ከጠፋ ‹ለኔ ቢጤ› እንድሰጥ ሆኜ ነው ያደግኩት፡፡ በልጅነታችን የምንጫወትባቸውን ድባና ቃጫ እንኳ ዛሬ ወድቆ ባለቤቱን ካገኘሁት እመለስ ነበር፡፡ የተገኘ ነው ለመባል አንድ እቃ ‹ጨለማ የነካው› (ጨለማ የነካው ማለት አንድ ሌሊት የማንም ሳይሆን ካደረና በቀጣዮቹ ባሉት ቀናት የተገኘ እቃ ለማለት ነው) መሆን ነበረበት፡፡ በልጅነቴ የተነገረኝ በተግበር ሳየው ሲጣረስ ጊዜ ይህን ጻፍኩ፡፡
ለመግቢያ ያክል ይህን ያክል ካልኩ የስነ ምግባር ችግር የምላቸውን አንድ በአንድ ለማየት እሞክራለሁ፡፡ በቅድሚያ ግን የሀይማት ተቋማት የሞራል ቀዳሚ አስተማሪ ስለሆኑ እንመለከታለን፡፡
1.   የሀይማኖት ተቋማት
‹አትስረቅ› ብሎ ያስተማራችሁ መምህር ሲሰርቅ ብትመለከቱ፣ ስለሰው ልጆች እኩልነት የሰበካችሁ እርሱ ጋንታ ሲለይ፣ የሰው ልጆችን እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ የሚለው ውስጡ በቂም የመገለ እንደሆነ ስትገነዘቡ ምን ይሰማችኋል!! እርግጥ ነው እነዚህ ግለሰቦች ራሳቸውን እንጅ የሀይማኖት ተቋሙን እንደማይወክሉ ግለጽ ነው፡፡ እኔ የምጽፈው የአየሁትን አሊያም እናንተ የምታውቁትን ሊሆን ይችላል -ግን ስንቶቻችን እንደሆነ አላውቅም፡፡ እስኪ አንዳንዶቹን አሁንም ዘርዘር አድርገን እንመልከት፡፡
1.1.  በታቦት ስም የሚለምኑ ሰዎች መበራከት
‹መዋሸት ሐጢያት ነው› እያለ የሚያስተምር፣ ስለስርቆት ወንጀልነት በየአብያተ ክርስቲያኑ የሚያስተምር ሰባኪ በየቦታው የቅዱሳንን ስዕል ዘርግቶ ‹‹እንዲህ የሚባል ቤተ ክርስቲያን ተቃጥሎ ለማሰራት … ከበረከቱ ተሳተፉ!!›› የሚል ጥሪ የሚሰጡ መንገድ ዘግተው የሚለምኑ ሰዎች በየከተሞቻችን መመልከት አዲስ አይደለም፡፡ በየቀኑ ቁጥራቸውም እየጨመረ ይገኛል፡፡ ከዚህ ላይ ለተባለው ዓላማ የሚለምኑ ሰዎች የሉም ማለት አይቻልም ግን በቁጥር አናሳ ይመስሉኛል፡፡ እያለው መለመን አንድ ችግር ነው ሲቀጥል ደግሞ በቅዱሳን ስም መለመን ሌላው ችግር ነው፡፡ እንበልና ያ የሚለምነው ሰው ገንዘብ ስለሌለው ብለን እንስብ፡፡ ታዲያ እንደኔ ቢጤዎች መንገድ ዳር ተቀምጦ መለመን ሲችል ስዕል ዘርግቶ ለሚለው ዓላማ የማይውልን ገንዘብ መሰብሰብ ‹ሐጢያትነቱ› ብዙ ነው፡፡ ውሸት አለበት፣ ስርቆት አለበት፣ አለመታመን አለበት፡፡ ለዚያውም ለእምነቱ በጣም ቅርብ ነኝ በሚለው ሰው (ለእምነቱ ቅርብ ያልሆኑ ሰዎች አስመስለው አይለምኑም ብሎ መደምደም አይቻልም)፡፡ ስጡ ይሰጣችኋል እያለ የሚያስተምረው ግለሰብ የሚሰበስበው ወደ ራሱ ኪስ ከሄደ ‹ቡራኬው› ምኑ ላይ ሊሆን ነው!! እነዚህን ግለሰቦች ማንም ወደ ህግ ሲያቀርባቸው አይታይም፡፡ የእምነቱ ሀላፊዎችም በእነዚህ ላይ ውግዘት ሲያደርጉ አሊያም ምዕመኖቻቸውን ሲያስተምሩ አይታይም፡፡ መስጠት አሪፍ ነው ብለን ስናስብ ለነማን መሰጠት እንዳለበትም ህዝቡን ማሳወቅ ያለብን ይመስለኛል፡፡  ለለመነ ሁሉ የሚሰጠው ከሆነ እና የሚለምኑ ሰዎች በአቋራጭ ሀብት የሚያካብቱበት አጋጣሚ ከበዛ ለማኝነትንም ማታለልንም አበረታታን ማለት ነው፡፡  ይህ ደግሞ የሚሆነው የግብረ ገብነትን ከሚያስተምሩት ወገን ሲሆን ችግሩን ለመፍታት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
1.2.  የንዋየ ቅድሳት ሽያጭ እና ስርቆት መበራከት
አስታውሳለው ከጥቂት አመታት በፊት በየመንገዱ ያለማንም ጠባቂ በደንብ ያልተቆለፉ ሙዳዬ ምጽዋት መስጫ ሳጥኖች ተተክለው ማዬት የተለመደ ነበር፡፡ አማኝም ያለውን ነገር ከዚያች አነስተኛ ሳጥን ውስጥ በደስታ ይጨምራል፡፡ ያችን ሙዳዬ ምጽዋት አይደለም መስበር ባለው ክፍተት የሳጥኗን መሙላት አለመሙላት መመለክት በራሱ በጠራራ ጸሀይ መብረቅ ወርዶ የሚመታን ይመስለን ነበር፡፡
አሁን በዱር የተቀመጠ ሳጥን አይደለም ከቤተ ክርስቲያን ጓሮ ያለ ሙዳዬ ምጽዋት እቃ ቤት ሳይቆለፍ በስህተት ቢያድር የሚፈጠረውን መገመት አያስቸግርም፡፡ የማይደፈሩ መስለው የሚታዩን ነገሮች ሁሉ በቅርብ ሰዎች ሲደፈሩ እናያለን፣ እንሰማለን፡፡ የአብያተ ክርስቲያናት ንብረት ብቻ ሳይሆን ጽላት ሁሉ የሚቸበችቡ ውስጥ አዋቂዎች የበረከቱበት ዘመን ላይ ነው ያለነው፡፡ በቀን ሰው በጨለማ ደግሞ ከአውሬ የባሱ ሰዎች ሞልተውናል፡፡ ቀን ላይ አውደ ምህረት ላይ ሲሰብኩ ላሳር፣ በቀለም እውቀታቸው የተደነቁ በግብር ግን ምንም የሌሉበት ሰዎች እንዴት ‹እምነት ያለስራ ከንቱ ነው!› ብለው ለመስበክ ሞራል የት አገኙ!! ቅርሳቸውንና ማንነታቸውን ለመሸጥ የማይደራደሩ ግለሰቦች እነርሱ እንዴት የሞራል አባት ሊሆኑ ይችላሉ!! እነዚህን ውድ ንዋዬ ቅድሳትና የሀገር ቅርሶችን ሊያሻሽጡ የሚችሉ ደላላዎች መበራከታቸው ለምን አይደንቅም!!  
የአራተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ አባቴ የት እንዳገኛት ባለውቅም አንድ ግጥም ነገረኝ፡፡ እኔም ከቤታችን በር ላይ በነጭ ጠመኔ ተየብኳት፡፡ ከ16 ዓመታት በኋላ ቤተሰብ ለመጠየቅ ስሄድ እስካአሁን ሳትጠፋ አገኘዋት፡፡ እንዲህ ትነበባለች!
ዝምድናም ተረሳ -ውለታም ባከነ
የሰው ሀይማኖቱ ገንዘብ ብቻ ሆነ!!
የሰውን ልጅ ገንዘብ ብቻ ሲነዳው ‹‹ለሁለት ጌታ አትገዙ›› እያለ የሚሰብከውን መምህር ገንዘቡ ሲገዛው አየን፡፡ ብዙ ሊባል ይችላል- ግን ምን ማድረግ ይቻላል!!
1.3.  የፍቅረ ቢጽ መጥፋት
ጓደኛህን እንደ ራስ ውደድ ብሎ ያስተማረ የሀይማኖት አባት እርሱን ያልመሰሉትን ሲያወግዝ፣ በሌሎች ላይ ሲዝት መመለከት የተለመደ ሆኗል፡፡ እኔ እስከማውቀው እርስ በርስ መዋደድን የሚኮንን እምነት ያለ አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ በክርስትና የሚጠሏችሁን ውደዱ ነው ዋናው ትዕዛዝ፡፡ የሚወደውን ማንም ይወዳል- የሚጠላውን መውደድ ከምንም በላይ እንደሆነ ነው መጽሀፍ የሚያዘው፡፡
ምንም እንኳ ይህ የብዙ ሰው ችግር ነው ብየ ባላስብም ልዩነትን የሚሰብኩ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደሉም፡፡ በየ ድረ ገጹ ሀይማኖትን መሰረት በማድረግ ጥፋትን የሚሰብኩ የድምጽና የቪዲዮ ምስሎች ለእልቂት የተላኩ ጊዜያቸውን ጠብቀው የሚፈነዱ ሚሳኤሎች ናቸው፡፡ በሜንጫ ጭፍጨፋን የሚሰብኩን የፖለቲካና የሀይማኖት ሰዎቻችንስ ከእኛው ጉያ የወጡ አይደሉምን!! መድረክ ሞቅ ባለጊዜ የሚናገሩትን የማያውቁ ሰዎች የራሳቸውን የውስጥ ጥላቻና ቂም በሀይማኖት ተቋሙ ስም የሚያደርጉት አንድ ሁለት ብሎ ከመቁጠር በላይ ተበራክተዋል፡፡
ያደገበትን እምነት ቀይሮ ወደ ሌላ የእምነት ተቋም በገባ ማግስት ከሚሄድበት ቤተ ጽሎት ከአመክንዮ ይልቅ የቀደመውን ቤቱን ሙልጭ አድርጎ የሚሰድብ ሰው ስንት ነው!! እምነት የግል ሆኖ ሳለ ‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል› እንዳለችው እኔ የሌለሁበት ቤት ባዶ ቀፎ ነው ብሎ መናገር ግብረ ገብነቱ የዜሮ ድምር ውጤት ነው፡፡
በዩንቨርሲቲዎች በየሀይማኖቱ ተቋማት የሚዘጋጁ የማጠናከሪያ ትምህርቶች አድሎ የበዛባቸውና የእበልጥ እበልጥ ፍክክር የሚታይባቸው ናቸው፡፡ ማጠናከሪያ ትምህርቱን የሚሰጠው መምህር አባል የሆነበት የእምነት ተቋም ውስጥ የሚማሩ ልጆች በዚያ የትምህርት ዓይነት ከሌላው እምነት አባል ከሆኑ ልጆች የላቀ ውጤት ያመጣሉ፡፡ አንዳንዴ እንዲያውም በመስጊድና አብያተ ክርስቲያናት ፈተናውን በውርክ ሽት መልክ የሚሰጡ መምህራኖችም ይገኛሉ አሊያም ቅሬታ የሚፈጠርባቸው ተማሪዎችም አሉ፡፡ 
1.4. አድርባይነት
አድርባይነት የሁሉም ሀይማኖት ተቋማት መለያ እየሆነ ነው፡፡ በተለይ በየጊዘው የሚመጡትን ገዥዎች ማወደስ ልማድ ነው፡፡ መጥፎም ይሁን ደግ መንግስት ዘመኑን ሲጨርስ በአንድ በሌላም ምክንያት ይቀየራል፡፡ ሀይማኖታዊ መጽሀፉ ግን የእግዚአብሄር ቃል ነው እና ያው ነው፡፡ በምንም መልኩ ዛሬ ያወደሰውን አገዛዝ የሚቀጥለው አመራር ሲመጣ ያለፈውን መኮነን ያለውን የማጽደቅ ስራ መሰራት አይችልም፡፡ የሀይማኖት ሰዎች ሁለት መልክ ሊኖራቸው አይገባም ነበር በመሰረቱ፡፡ በደርግ ዘመን ደርግን የደገፉ ደርግ ሲወድቅ ደርግን ጭራቅ ሰወ በላ ብለው ኢህአዴግን የሚቀድሱ የሀይማኖት ተቋማት ነው ያሉን፡፡ እርግጥ ነው ግለሰብ በአመለካከት ሊለያይ ይችላል ግን የግለሰቦች አስተያየት በተቋም ደረጃ ሲሆን አስቸጋሪ ነው፡፡
በክርስትናውም በእስልምናውም የሀይማኖት ያሉ መሪዎች ኢህአዴግ ሰልፍ ሲጠራ ሀይማኖታዊ ንዋየ ቅድሳትን ይዞ መውጣት የተለመደ ባህል ሆኗል፡፡ መንግስት ደግ ሲሰራ ይህን መንግስት ያኑርልን ብሎ መጸለይ ነውር አይደለም፡፡ ግን ደግሞ ሲሳሳትም መንቀፍ መለመድ ነበረበት፡፡ ዜጎች ሲፈናቀሉ፣ ያለስራቸው ለእስር፣ እንግልትና ሞት ሲዳረጉ፣ በእምነት ተቋማት አድኑኝ ብለው ሲጠለዩ አሳልፎ መስጠትና ማጨብጨብ ከምን የመጣ ነው!!
እኔ ሁሌ የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ አሁን በተለይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰላማዊ ሰልፍ መጥራት ከጀመሩ ወዲህ ኢህአዴግም እንዲሁ ማድረግ ጀመረ (ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ፓርዎች በፍጥነት የቀሰማት ምርጥ ተመክሮ)፡፡ ታዲያ ሀይማኖትን ወክለው በሰልፍ የሚገኙ የሀይማኖት አባቶች ጉዳይ ያሳስባል፡፡ የአንድ እምነት ምዕመን በሙሉ እንዴትም ቢሆን የአንድ ፓርቲ ደጋፊ ሊሆን አይችልም፡፡ እንኳን አሁን መንግስትና ሀይማኖት በህግ በተለዩበት ዘመን ቀርቶ በጃንሆይ ዘመንም ቢሆን ሁሉም ክርስቲያን ጃንሆይን ይደግፋል ማለት አይቻልም፡፡ ታዲያ የሀይማኖት ተቋምን ወክለው ሰልፍ የሚወጡ ሰዎች በምን ሂሳብ አደረጉት!! ቢሆንስ የአብያተ ክርስቲያናት ንዋዬ ቅድሳት ለምን የሰልፍ ማድመቂያ ይሆናሉ!! የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሄርን ለእግዚአብሄር እንዲል መጽሀፉ፡፡ ጥላውም ጸናጽሉም በስለት ያስገባው ይኸው ምዕመን ነውና፡፡ የገባው ደግሞ ለአምላክ ማወደሻ ልክብሩም መውረሻ እንጅ ኢህአዴግን ለማመገሻ አይመስለኝም፡፡ ይህ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡
1.5.  ጎሰኝነት
አንድ ወቅት ካርቱም መድሀኒዓለም ቤተክርስቲያን ሂጄ ይህን ታዘብኩ፡፡ በሱዳን ብዙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ከስደተኞቹም አንድ ዲያቆን አገኘውና ተጫወትን፡፡ ዲያቆኑ ካርቱም ከአንድ ዓመት በላይ ኖሯል፡፡ እንዲቀጥሩት ይፈልጋል- ግን የቤተ ክርስቲያኑ ቆሞስ ክፍተት ሲኖር ከአካባው ሰዎች በማስመጣት ብቻ እንዲቀጠሩ እንደሚያደርግ አጫወተኝ፡፡ አዘንኩ - አንደኛ በሚደረገው ሁለተኛም ልጁ አሳዘነኝ፡፡ ከዚሁ ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያውያኝ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት አለ፡፡ ቅጥሩ የሚፈጸመው ግን በተመሳሳይ እንዲሁ ከቀያቸው በሚመጡ ሰዎች ነው፡፡ ይህ በእውነት በክርስቶስ አንድ ነን እያሉ ለሚያስተምሩ ሰዎች በቤታቸው ይህ መኖሩ ያሳዝናል፡፡ እንደሚሰማው በምዕራብ ሀገራት ባሉ ብትን ወጎኖች /ዲያስጶራዎችም ይህ ነገር የገነነ ነው፡፡
አዲስ አበባ ያለ አንድን ደብር ማየት በቂ ነው፡፡ አስተዳዳሪው ከየት አካባቢ እንደሆነ ማየት ቀሪዎቹ አገልጋዮች የየት አገር ሰዎች እንደሆኑ መገመት አይከብድም፡፡ ክፍለ ሀገርም ወጣ ቢባል ከዚህ የተለየ አይሆንም፡፡ 
እንደ አጠቃላይ የእምነት ተቋማትን በዚሀ መልክ መጀመሪያ ማዬቴ የሞራል ቀዳሚ አስተማሪዎች ሆነው በሞራል እጦት ሲታመሱ ስመለከት ምዕመናኑ ሞራል የሌላቸው ቢሆኑ ብዙም የሚደንቅ አይደለም በማለት ይህን ጻፍኩ፡፡ የአሳ ግማቱ ከጭንቅላቱ ነው እንዲሉ፡፡ ክርስትና ሀይማኖትም ላይ ያተኮርኩት ከሌሎች የእምነት ተቋማት የተሻለ ስለማውቀው መሆኑ ይታወቅልኝ እንጅ ሌሎች ሀይማኖቶችም የዚህ ሰለባ አይደሉም ለማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ከምዕመን የማይጠበቅ ሀይማኖታዊ ዶግማና ቅኖና ተላልፌ ብገኝ የተሳሳትኩት በአለማወቅ እና በቅንነት እንጅ በድፍረት አሊያም በር ለመቅደድ ፈልጌ እንዳልሆነ በእግዚአብሄር ስም እናገራለሁ፡፡
በሚቀጥለው ሳምንት የዚህን ትውልድ እና የመንግስት ተቋማትን የሞራል ዝቅጠት ምን ያህል እንደከፋ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡  ይቀጥላል…….
መልካም አዲስ አመትና ሳምንት